ወጣቱ የፍቼ ጫምባላላን ባህላዊ ስርዓት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ተመለከተ

75
ሃዋሳ ሰኔ 5/2010 ወጣቱ አባቶች በክብር ጠብቀው ያቆዩትን የፍቼ ጫምባላላን ባህላዊ ስርዓት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት የሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝምና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ አሳሰበ፡፡ የሲዳማን የዘመን መለወጫ በዓል ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበር እየተሰራ መሆኑን  ፖሊስ አስታውቋል፡፡ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ ለኢዜአ እንደገለጹት የፍቼ ጫምባላላን ባህላዊ ስርዓት መገለጫ ከሆኑት መካከል ፍቅር፣ አንድነት፣ እርቅ፣ መከባበርና አብሮነት ይገኙበታል፡፡ ባህላዊ ሰርዓቱ በተባበሩት መንግስታት በዓለም የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡን አስታውሰው አባቶች በክብር ጠብቀው ያቆዩትን ይህንኑ  ስርዓት እንዳይበረዝ የአሁኑ ትውልድ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት ስለስርዓቱ መረጃው በሰነድ የሚገኝ በመሆኑ ወጣቶች አንብበውና ተረድተው በዓሉን በእውቀት ሊያከብሩት ይገባል፡፡ ከበዓሉ መገለጫ ውጭ  ያልተገባ ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦች ከድርጊታቸው  መታቀብ እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡ የሃዋሳ ከተማ አስተዳዳር ፖሊስ መምሪያ ማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር ደረሰ ቡሳሮ በበኩላቸው  በዓሉ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበር በየደረጃው ከሚገኙ የህግ አስከባሪዎች ጋር አቅደው  እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የከተማው ህዝቡ ከፖሊስ ጎን በመቆም ለራሱ ሰላምና ፀጥታ ዋና ተዋናይ እንዲሆንም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ከሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ  መሰረት ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት ከተማዋ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማዕከል በመሆኗ በዓሉ በሰላም ፣በአንድነትና በፍቅር እንደሚያከብሩት ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ የበዓሉን ስርዓት ያልተረዱ ግለሰቦች  የማይገባ ተግባር እንደሚስተዋልባቸው ጠቁመው በዓሉ የአንድነትና የተጣላ ጭምር የሚታረቅበት  ስርዓት መሆኑን  በመገንዘብ ለስኬታማነቱ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ በዓሉ በአደባባይ የሚከበርና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የሚሳተፍበት በመሆኑ በሰላም እንዲጠናቀቅ በተለይ ወጣቱ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ደግሞ  ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ አክሊሉ አርጎ ናቸው፡፡ የፈቼ ጨምበላላ ዛሬ ማምሻውን በሚከናወነው የዋዜማ በዓል "ፊቼ" ይጀመራል፤ ነገ ደግሞ ጫምባላላ (የዘመን መለወጫ በዓል ) በድምቀት ይከበራል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም