በአረንጓዴ አሻራ ቀን ልማት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን የሐረሪ ፣ወላይታ እና አጋሮ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

66
ሐረር /ሶዶ/ጅማ ኢዜአ ሐምሌ 19 ቀን 2011 በአረንጓዴ አሻራ ቀን ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ለመንከባከብ መዘጋጀታቸውን በሐረሪ ክልል ፣ ወላይታ እና አጋሮ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ። በእነዚህ አካባቢዎች በዕለቱ ከ1 ሚሊዮን 200ሺህ በላይ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል። አርሶ አደር አባድር ሳዲቅ በሐረሪ ክልል የሐኪም ጋራ ነዋሪ በመሆናቸው በአካባቢያቸው ለበርካታ ጊዜ ችግኝ ተከላን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን በሰጡት አሰተያየት ተናግረዋል። በተለይ በአሁኑ ወቅት መንግስት ያቀደውን የችግኝ ተከላ ዘመቻን ለማከናወን ከመቼውም በበለጠ ዝግጁ እንደሆኑም አስረድተዋል። "በአካባቢው የምንገኘው ሰዎች 4ሺ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ቆፍረን በማለስለስ ዝግጁ አድርገናል" የችግኝ አቅርቦትም ወደ አካባቢው እየመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል። "እስካሁን በግሌ 20 ጉድጓድ  ቆፈሬያለው ቀሪ 20 ጉድጓድ በዚህ ሁለት ቀን በማጠናቀቅ 40 ችግኞችን ለመትከል ተዘጋጅቻለው " ያሉት ደግሞ በአቦከር ወረዳ ቀበሌ 13 ነዋሪ አቶ ዘከርያስ አባስ ናቸው። የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሻሚ አብዲ እንደገለጹት በክልል በክረምት ወራት እርጥበትን በመጠበቅ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ አርሶ አደሮች ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ችግኞች በመተከል ላይ ይገኛል። እስካሁንም በክልሉ ገጠርና ከተማ   በተከናወነው ስራ 700ሺ ችግኞች ተተከልዋል። ሐምሌ 22 ቀን 2011  የአረንጓዴ አሻራ ቀን 200 ሺ.ችግኞችን በአንድ ቀን ለመትከል  የመትከያ ጉድጓድ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ዕለት በነቂስ በመውጣት በልማቱ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ገልጸዋል፡፡ በዕለቱም ከ30 ሺህ በላይ የተለያየ ዝሪያ ያላቸው ዕጽዋቶች እንደሚተከሉ ዩኒቨርሲቲዉ አስታውቋል፡፡ በዩኒቨረሲቲዉ የሶሾዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ደጉ ጳዉሎስ እንዳሉት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተጀመረው የችግኝ ተከላ ላይ በነቃት  እየተሳተፉ መሆናቸውና በአረንጓዴ አሻራ ቀን ለመድገም ዕለቱን  እየተጠባበቁ ነው፡፡ በአረንጓዴ አሻራ ዕለት ለአካባቢው ማህበረሰብ ምሳሌ ለመሆን ከጠዋቱ 12 ተኩል  ጀምሮ በመውጣት ችግኝ ለመትከል መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲዉ የኦዲት ክፍል ዳይሬክተር ወይዘሮ ውድነሽ ካሳ ናቸው፡፡ የዩኒቨርስቲው ኮሙኒኬሽንና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ኤርምያስ በበኩላቸው የተቋሙ ማህበረሰብ በዕለቱ  ከ30 ሺህ በላይ ችግኞች መትከል እንዲችሉ የግንዛቤ ማስጨበጥ፣ የቦታ መረጣና የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አባላት ካለፈው ሰኔ  ወር ጀምሮ  ከ50 ሺህ በላይ የተለያየ ዝሪያ ያላቸው  ችግኞች መተከላቸውም ተመልክቷል፡፡ በአረንጓዴ አሻራ ቀን ችግኝ ከመትከል ባሻገር  የተተከለውን በዘላቂነት በመንከባከብ ለማልት ዝግጁ መሆናቸውን  አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአጋሮ ከተማ 1 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን  የከተማው አስተዳደር አስታውቋል። የአስተዳደሩ ከንቲባ  አቶ ኢሊ ስ ሸረፉ እንዳሉት  ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም  የሚተከሉት እነዚህ ችግኞች በፓርክ፣ በመካነመቃብር ስፍራዎች፣ በተለያዩ ተቋማት ግቢ ውስጥ እና በተራቆቱ አካባቢዎች በተዘጋጁ ጉድጓድ ነው። እስካሁን ባለው ሂደት  የከተማው ነዋሪዎች ከ100 ሺህ በላይ ችግኝ መትከላቸውን አመልክተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም