ለትውልድ የሚተርፍ አሻራ

129

በሃብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ)

የዛፍ መትከል ባህል ጥንትም  የነበረ ልማድ መሆኑን የታሪክ ድረሳናት ያስረዳሉ። ጥንታውያን ግሪኮችና ሮማውያን ዛፍ መትከል ሰፊ ልማድ እንደነበራቸው ይነገራል። ሮማውያኑ በጥንተ ዘመናቸው የነበራቸውን የችግኝ አተካከል ጥበብ በመዛግብት አኑረውት ለዚህኛው ትውልድ አስተላልፈውታል። የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች አቆፋፈር፣ የተክሎች ስር አጠባበቅ፣ የዛፍ ችግኞችን በቀለማት የመለየት ዘዴን፣ የሚተከሉ ችግኞች ከፀሃይና ከንፋስ ጋር የሚኖራቸውን ዝምድና እና ሌሎች ዘዴዎችን ሮማውያኑ ለአሁኑ ትውልድ አሻግረዋል። በተጨማሪም ሮማውያኑ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ወደ ብሪታኒያ እንዳመጡም ታሪክ ይመሰክርላቸዋል። ሮማውያኑ የአትክልተኛነት ጥበብን የተካኑ እንደነበሩም ድርሳናቱ ያስረዳሉ።

በጥንታዊ ስልጣኔ ውስጥ ያለፈችው ሃገራችንም ከግሪክ እና ሮማውያኑ ባልተናነሰ ሃገር በቀል የዛፍ ዝርያዎችን ጠብቆ ከማቆየት ጋር የተዛመደ ታሪክ አላት። አጤ ምኒሊክ በዘመነ መንግስታቸው ወቅት የባህር ዛፍ ዝርያዎችን ከአውስትራሊያ በማስመጣት በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እንዲተከሉ የማድረጋቸው ታሪክ ከችግኝ ተከላ የዘመቻ መርሃ ግብር ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችል በ1886 ዓ.ም የተከወነ ታሪክ ነው። የባህር ዛፍ የሚለው ስያሜንም ዛፉ ከባህር ማዶ ወደ ሃገር ቤት ከመግባቱ ጋር ተያይዞ እንዳገኘ ታሪክ ይነግረናል። ምኒሊክ የዛፉ ችግኝ ተፈልቶ ለአቅመ መተከል ከደረሰ በኋላ ህዝቡ ችግኙን እየወሰደ እንዲተክል በማሰብ “የባህር ዛፍ የተተከለበትን መሬት ግብሩን ምሬያለሁ” የሚል አዋጅ አውጥተው ህዝቡ በሽሚያ የዛፍ ችግኞችን እየወሰደ መትከል መጀመሩና በጊዜው ችግኙ ተወዶ አርባ ችግኝ በአንድ ጥሬ ብር እንደተሸጠ ዻውሎስ ኞኞ አጤ ምኒሊክ በሚለው መፅሃፉ ላይ ከትቦታል። ሃገራችን ችግኝ አፍልቶ ዛፍ የመትከልን ታሪክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ባህል ብታደርግም የተለያዩ ሃገር በቀል ዛፎችን ጠብቆ የማቆየት ከመቶዎች አመታት የተሻገረ ልማድ አላት። በአብያተ ክርስቲያናት፣ በጥንታዊ መስኪዶች እና በነገስታት አፀድ የሚገኙ ዕድሜ ጠገብ ዛፎችን መመልከቱም ለዚህ ሃቅ ምስክር ሊሆን ይችላል።

ከዚያም በኋላ በየጊዜው የመጡ የመንግስት አስተዳደሮች የተለያዩ መርሃ ግብሮችን በመንደፍ የችግኝ ተከላ ተግባሩን ሲፈፅሙት ቆይተዋል። በአፄ ሃይለስላሴ፣ በደርግ እንዲሁም በኢህአዴግ የስልጣን ዘመናት በተለያዩ መሪ መልዕክቶች ሰፋ ያሉ የችግኝ ተከላ ዘመቻዎች ተካሄደዋል። ከሃገራችን የቆዳ ስፋት 40 በመቶ የሚሆነው ክፍል በደን የተሸፈነ እንደነበር በታሪክ የምናውቀው ሃቅ ቢሆንም ይህ አሃዝ ወደ ታች አሽቆልቁሎ 3 በመቶ ደርሶ እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ከምዕተ አመቱ መግባት ጋር ተያይዞ 2000 ዓ.ም በተከናወነ የቅስቀሳ ስራ በዘመቻ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ወደ 3 በመቶ ወርዶ የነበረውን የሃገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 15 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል። ይኸው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መዲናችንን የከበቡ ገላጣ ተራሮች መልሰው እንዲያገግሙ ማድረጉንም በጊዜው በየካ እና ሌሎች ጋራዎች ላይ የታየው ለውጥ ምስክር ነው።

አሁን ደግሞ ኢትዮዽያ 4 ቢሊዮን የዛፍ ችግኞችን ለመትከል ውጥን ይዛ እንቅስቃሴ ከጀመረች እንሆ ወራት ተቆጠሩ። አንድ ግለሰብ 40 ችግኞችን የመትከል ዕቅድ ይዞ ተግባሩን እንዲወጣም ሃገሪቱ ሃላፊነቱን ሰጥታዋለች። በዚህ የዛፍ መትከል ዘመቻ 400 ሺ ሄክታር መሬት በዛፍ ለመሸፈን እንደታቀደ የግብርና ባለሙያዎች ተናግረዋል። ሃምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ትልም ተነድፎ የችግኝ ዝግጅትና የጉድጓድ ቁፋሮዎች ተከናውኗል። በዕለቱ ሁሉም ዜጋ የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት ቀኑን በጉጉት እየጠበቀው ይገኛል። ይህንን የዛፍ መትከል መርሃ ግብር ከዚህ ቀደም ሲከናወን ከበነረው የሚለየው እንደየአካባቢው ሁኔታ ተስማሚ የሆኑ የዛፍ ችግኞች ፈልተው መሰናዳታቸው ነው። ስራው የበርካቶችን ድጋፍ ከማግኘቱም በዘለለ ከዚህ ቀደም ባልታየ ቅንጅት ለማከናወን መታሰቡም ለየት እንደሚያደርገው ተነግሯል። የሃገራችንን ከብዙ በጥቂቱ በዚህ መልኩ ከተመለከትን አህጉራዊና አለም አቀፍ የዛፍ መትከል ታሪኮች ምን ልምዶች ተቀምረውባቸዋል? ምንስ የሚነግሩን ጉዳይ አላቸው? እንመልከታቸው።

በቅርቡ የጀርመኑ ዶቼ ቬሌ ‘The Man Greening Burkina Faso’s Desert’ በሚል ርዕስ የቡርኪና ፋሶ ዜጋን ጠንካራ የደን ልማት ታሪክን ያዘለ አስገራሚ መረጃን አሰራጭቷል። ያኩባ ሳዋዶጎ የተባለው ቡርኪናፋሶአዊ የ80 አመት አዛውንት እኤአ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ በሃገሩ በረሃማነትን ለመግታት በሚል አጋዥ ሳይኖረው ብቻውን የዛፍ መትከል ተግባሩን ይጀምራል። ከተጠቀሰው ጊዜ ጀምሮ የሳዋዶጎን ልፋት የጠየቀው የዛፍ መትከል ስራ እንሆ አሁን ፍሬ አፍርቶ ለአካባቢው ጥላን፣ ለመኖሪያው ጥሪትን አምጥቶለታል። ያኩባ ሳዋዶጎ የሚኖርባት ጎርካ የተባለችው መንደር አሁን የበረሃ ገነት ሆናለች። ለለምለሚቷ የሳዋዶጎ መንደር ምስጋና ይግባና የአካባቢው ነዋሪ ቢርበው ምግቡን፣ ጤናው ቢታወክ የባህል መድሃኒቱን ከዛፎቹ ያገኛል። ያኩባ ሳወዶጎም 27 ልጆቹን እና የልጅ ልጆቹን በምግብ እና በህክምና ይንከባከባል። ‘ጎርካ’ የተሰኘችው መንደርም የችግኝ አፈላል፣ አተካከልና እንክብካቤ ስልጠና የሚሰጥባት መንደር ሆናለች። ሳዋዶጎም በዚህ ተግባሩ የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ ሊሆን ችሏል።

እኤአ በ1870ዎቹ አካባቢ ስቴፈን ስሚዝ የተባለ አሜሪካዊ ሃኪም በኒውዮርክ ከተማ ዛፍ እንዲተከል ሰፊ ቅስቀሳ ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ። እንደ መረጃዎቹም ስሚዝ በወቅቱ ሰዎች ዛፍ እንዲተክሉ ካነሳሳበት ጉዳይ አንዱ ከመጠን ያለፈ ሙቀት የሰው ልጆችን ህይወት ሊቀጥፍ እንደሚችል እና ዛፍ በመትከል ግን ተፅዕኖውን መቀነስ እንደሚቻል በማስተማር ነበር። ዛፎችን በመትከል ብቻ በሙቀት ሳቢያ የሚገጥመንን የጤና መታወክ ከመቀነሱም ባሻገር በአመት (ከያኔው አሃዝ አንፃር) ከ3ሺ እስከ 5ሺ የህፃናት ህይወትን መታደግ እንደሚቻል ስሚዝ አዘውትሮ ያስተምር ነበር። ከማስተማርም በዘለለ ስሚዝ የተለያዩ መፍትሄ አፍላቂ ጥናቶችን በማውጣት ለዘርፉ ባለሙያዎች እንዳበረከተም መረጃዎቹ አስረድተዋል።

 

ልክ እንደ ያኩባ ሳዋዶጎ እና ስቴፈን ስሚዝ ያሉ በግለሰብ ደረጃ መሰል ተግባራትን የፈፀሙ ሰዎችን በሃገራችን ይገኛሉና ተግባራቸውን በማውጣት ሌሎች እንደ እነርሱ አይነት ሰዎች እንዲበዙ መስራት ይጠበቅብናል። ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በተያያዘም ‘ናሽናል ጂኦግራፊክ’ የዛፍ ችግኝን ጥቅም ላይ አውለው አለማችንን ያስደመሙ ሰዎች አምስት አጋጣሚዎችን በእትሙ ይዞ ወጥቷል፤ ቀጥለን እንመልከታቸው።

 

  1. ከ14 ቢሊዮን በላይ ዛፎችን የተከለው ታዳጊ

ታዳጊው ፌሊክስ ፊንክቤይነር ይባላል። ፊንክቤይነር ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ለመዋጋት በሚል ከህፃንነቱ ጀምሮ ዛፍ ሲተክል መቆየቱን መረጃው ጠቁሟል። የዘጠኝ አመት ልጅ ሳለ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመገኘት በዕድሜ በሰል ያሉ ሰዎች ለመጪው ትውልድ በሚል ዛፍ ሲተክሉ በማየት ተግባሩን ለመከወን መነሳሳቱን ተናግሯል።

በልጅነት ዕድሜው ጉዳዩን ከቀልቡ የፃፈው ፊንክቤይነር ከጓደኞቹ ጋር ‘ፕላንት ፎር ዘ ፕላኔት’ የሚል ቡድን በመመስረት የመንግስታቱ ድርጅት የነደፈውን የቢሊዮን ዛፍ ዘመቻ (UN’s Billion Tree campaign) በአጋርነት ለመተግበር ተቀላቅሏል። የታዳጊው የችግኝ ተከላ ቡድንም በአለማችን አንድ ትሪሊዮን የዛፍ ችግኞችን የመትከል ትልም ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ይህም በምድር ላይ የሚኖረው እያንዳንዱ ግለሰብ 150 ችግኞችን እንዲተክል የማድረግ ውጥን በቡድኑ ተቀምጧል።

  1. ደን ፈጣሪው ህንዳዊ

ጃዳቭ ፓዬንግ በሚል የመዝገብ ስም የሚታወቀው ህንዳዊው እኤአ ከ1979 ዓ.ም አንስቶ የመሸርሸር ስጋት በተጋረጠባት ደሴት ላይ በርካታ የዛፍ ችግኞችን ሲተክል ኖሯል። በሰሜን ምስራቅ ህንድ የምትገኘው የማጁሊ ደሴት በአለማችን በወንዝ ከተከበቡ ደሴቶች ትልቋ ናት። 150 ሺ ለሆኑ ሰዎች መኖሪያም ናት ደሴቷ። ‘ብራህማፑትራ’ በሚል ስያሜ የሚታወቀው ወንዝ የአየር ንብረት ለውጥ ባመጣው ተፅዕኖ ሳቢያ የደሴቷን አፈር በየጊዜው ጠራርጎ ይወስድባታል። እኤአ ከ1917 ጀምሮ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የደሴቷ ክፍል በወንዙ ተጠርጎ ተወስዷል።

ሆኖም ጃዳቭ ፓዬንግ ችግሩን ለመቅረፍ በሚል በርካታ ዛፎችን በመትከል በአሜሪካ ማንሃተን ከሚገኘውና ‘ሴንትራል ፓርክ’ በሚል ስያሜ ከሚታወቀው የበለጠ ደን በመፍጠር አካባቢውን የበረሃ ገነት አድርጎታል። በፓዬንግ ብርታት የተፈጠረው ደን በአሁኑ ወቅት የዝሆኖች፣ የነብሮች፣ የአውራሪሶች እንዲሁም ሌሎች እንስሳት መኖሪያ ሆኗል። ፓዬንግ በተከላቸው ዛፎች መሬቱን ከመሸርሸር እንደጠበቀው ሁሉ አሁን ደግሞ ለመመንጠር ስጋት ከሆኑት ሰዎች እየጠበቀው እንደሚገኝ መረጃው አክሏል።

  1. የፍራፍሬ ችግኞችን ለአሜሪካ ያስተዋወቀው ግለሰብ

ዴቪድ ፌርቻይልድ በ1900ዎቹ በአሜሪካ የምግብ ተመራማሪ በመሆን ያገለግል ነበር። በጊዜው ለአሜሪካ እንግዳ የነበሩ ፍራፍሬዎችን እና ሌሎች ተክሎች ከውጪ እንዲገቡ አድርጓል። ዴቪድ የአቮካዶ፣ የማንጎ፣ የጃፓን ባለ አበባ የምግብ ፍራፍሬዎች እና ሌሎች ዝርያዎችን ወደ ሃገረ-አሜሪካ እንዲገባ ቀዳሚውን ሚና ተወጥቷል።

በጃፓን ቆይታው ወቅት የተማረከባቸውን የአበባና የፍራፍሬ ዝርያዎች ወደ አሜሪካኗ ሜሪላንድ ግዛት እንዲመጣ ያደረገው ዴቪድ እሱ ለሚኖርባት ቼቪ ቼዝ ከተማ ደግሞ 300 ዝርያዎችን በስጦታ አበርክቷል።

የአሜሪካ የኮንግረስ ምክር ቤት በወቅቱ ነዋሪዎቿን እምብዛም የማትማርከውን ዋሺንግተን ለማስዋብ ዘመቻ ባስቸመረበት በዚያን ወቅት ዴቪድ ፌይርቻይልድ በከተማዋ ቲዳል ቤዚን በተባለው አካባቢ ከጃፓን ያመጣውን ማራኪና አበባማ የቼሪ ዛፍ በመትከል ተሳትፎ አድርጓል። እግረ መንገዱንም ወደ ነጩ ቤተመንግስት ጎራ በማለት አሜሪካ ከጃፓን ጋር የነበራትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንድታሻሽል በመነጋገር በሺዎች የሚቆጠሩ የመሰል ዛፍ ችግኞች በትዕዛዝ እንዲመጡ አድርጓል። ዴቪድ ፌይርቻይልድ ከጃፓን ያመጣቸው ማራኪ ዛፎች ከመቶ አመታት በላይ በዘለቀ ቆይታቸውም የዋሽንግተን ዲሲ ከተማን እንዳደመቋት ይገኛሉ።

  1. ለገና ዛፍ ህይወታቸውን አደጋ ላይ የጣሉ የአንድ መንደር ነዋሪዎች

“ኖርድማን ፊር” የተባለው በአውሮፓ እጅግ ተፈላጊ የሆነው የገና ዛፍ ፍሬ በአሜሪካ ጆርጂያ ክልል በሚገኝ ራቻ ተብሎ በሚጠራ በደን የተሸፈነ ተራራ አናት ላይ ይበቅላል። ዛፉ ያለበት የተራራ አናት ላይ ወጥቶ ፍሬውን ለመሰብሰብ እጅግ አስቸጋሪ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ሰዎች በገድል የታጀበ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ ያስገድዳል። በተራራው አቅራቢያ ኑሮአቸውን የመሰረቱ የመንደሩ ነዋሪዎች ካለአንዳች የመሳሪያ እገዛ የዛፉን ፍሬ ለመልቀም ከተራራው አናት ላይ መገኘት የሰርክ ተግባራቸው ነው።

ነዋሪዎቹ ‘ለማን ይድላው ብለው ነው’ አሳራቸውን የሚበሉት ብለው ሳይጠይቁ አይቀርም እንበልና መቼም ዝም ብሎ ህይወትን አደጋ ላይ መጣል ሊታሰብ አይችልምና! ነገሩ ወዲህ ነው። ነዋሪዎቹ የሰበሰቡትን ፍሬ በኪሎ 90 የአሜሪካን ሳንቲም ችግኞችን ለሚያፈሉ ኩባንያዎች ይሸጣሉ። በዚህም ቀላል የማይባል  ገቢ ያገኛሉ። የገንዘቡን አነስተኛነት ከቢዝነሱ አደገኛነት አንፃር ሚዛን ላይ የሚያስቀምጡ ጉዳዩ ይመለከተናል የሚሉ አካላት የነዋሪዎቹ በተራራ አናት ላይ መገኘት ትኩረት የሚሻ ሁነት እንደሆነ ሲወተውቱ እስካሁን አሉ። የገና ዛፍን ወደ ቤት ለማምጣት በሚል ህይወትን ወደ ሞት አፋፍ ማድረስ እብደት ነው፤ ሲሉም አስተያየት ይሰጣሉ።

  1. የለንደን ከተማን ግዙፍ የዕፅዋት ማዕከል ለማድረግ የተለመው ግለሰብ

የናሽናል ጂኦግራፊክ አሳሹ እናም ራሱን ‘ጎሪላ ፎቶግራፈር’ ወይም ሽምቁ ፎቶ አንሺ እያለ የሚጠራው ዳንኤል ራቭን ኤሊሰን ለንደንን ግዙፍ የዕፅዋት ማዕከል ለማድረግ የግድ ራሱ ዛፍ መትከል እንደማይጠበቅበት ይናገራል። እሱ በሚኖርባት ለንደን ከተማ ላይ የተተከሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎችን በመመልከት ከተማዋን ግዙፍ የዕፅዋት ብሄራዊ ፓርክ የሚል አዲስ ስያሜን እንድታገኝ ሃሳብ አውጠነጠነ።

ከተማዋን ብሄራዊ ፓርክ የሚል ስያሜን በማጎናፀፍ በአለማችን የሚኖሩ ህዝቦች የሁል ጊዜ አኗኗር ውስጥ በርካታ መሰል የተቀናጁ ፓርኮችን መፍጠር የሚያስችል ራዕይን ማኖር እንደሚቻልም ራቭን ኤሊሰን ተስፋ ያደርጋል። የራቭን መኖሪያ የሆነችው ለንደን 47 በመቶዋ አረንጓዴ እና የተሰባጠሩ የዕፅዋት ዝርያዎች የሚገኙባት ከተማ ናት። እናም ራቭን ኤሊሰን ከተማዋ ይህንን እሴቷን ወደ ውጪ እንድታወጣ በማበረታታት የውጭው አለም ከተፈጥሮ ሊያገኝ የሚችለውን ጠቀሜታ ማጋራት ህልሙ ነው።

ለማጠቃለል ያህል

ከላይ ከዛፍ ልማት ጋር የተያያዘውን የኋላ ዳራ በማንሳት በአረንጓዴ ልማት ውስጥ የጠንካራ ግለሰቦች ሚናን በማንሳት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በአለም ላይ ሊነሱ ከሚችሉት አበይት ጉዳዮት ከብዙ በጥቂቱ የተጨለፈውን አስደማሚ ታሪኮች ተመለከትን። በታሪኮቹ ውስጥም አከባቢን በዕፅዋት በመሸፈን መንከባከብ ሊኖረው የሚችለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ለማየት ተሞክሯል። አለማችን በዚህ ወቅት ለችግኝ ተከላው ሰፊ ትኩረት መስጠቷም ጉዳዩን ከማጠናከር የዘለለ ፋይዳ የለውም። ባለፈው አመት መጋቢት ወር ላይ የመንግስታቱ ድርጅት ለከፋ ከባቢያዊ ጉዳት የተጋለጡ አካባቢዎች እንደገና እንዲያገግሙ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮግራም ይፋ አድርጎ ነበር። ይህም እኤአ በ2030 ዓ.ም 350 ሚሊዮን ሄክታር መሬት (በስፋት ከህንድ የሚልቅ) እንደገና እንዲያገግም የማድረግ ስራ እንደሚሰራ የተወጠነበት ነው። ህንድ በበኩሏ በ2020 የደን ልማት ዕቅድ 13 ሚሊዮን ሄክታር የመሬት ክፍሏን በደን ለመሸፈን አቅዳለች። በ2030 ደግሞ ላቲን አሜሪካ 20 ሚሊዮን ሄክታር እንዲሁም አፍሪካ 100 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በደን ለመሸፈን ትልም ይዘዋል።

ሃገራችንም በተያዘው ክረምት 4 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት ለመሸፈን ዕቅድ ይዛለች። እስካሁን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞች የተተከሉ ቢሆንም ወደታቀደው የተጠጋ ቁጥር ላይ እንገኛለን። ሃምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ‘የዜጎች የአረንጓዴ አሻራ ቀን’ በሚል መሪ መልዕክት በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ኢትዮዽያ በአለም አቀፍ ደረጃ አዲስ ክብረ ወሰን ለማስመዝገብ ዝግጅቷን አጠናቃለች። በዕለቱም ከችግኝ መትከል የዘለለ ትኩረት የሚቸረው ጉዳይ እንደማይኖር የመገናኛ ብዙሃኑ መረጃ ሲሰጡበት የቆየ ጉዳይ ነው። በዚህ ዕለት ሁሉ ዜጋ በተዘጋጀለት ቦታ በመገኘት ወዲህ የዜግነት ግዴታውን ይወጣ ወዲያ ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ አሻራውን ያኑር እንላለን።