ክልሎቹ በጸጥታ ጉዳዮ ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ

51
ሐምሌ 18 / 2011 (ኢዜአ)የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና በሱዳን የብሉ ናይል ግዛት በአጎራባች አካባቢዎች የፀጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ ፡፡ ስምምነቱን የተፈራረሙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰንና የብሉናይል ግዛት አስተዳዳሪ ሜጀር ጀኔራል አህመድ አብዱራሂም ናቸው፡፡ ክልሎቹ የተፈራረሙት 20 ነጥቦች የያዘው ስምምነት ዓላማ የክልሎቹን አጎራባች አካባቢዎች ፀጥታና ሠላም በማረጋገጥ የሕዝቦችን የልማት ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ ተመልክቷል፡፡ ከስምምነቶቹ መካከል ህገ-ወጥ የሰውና የአደንዛዥ እጽን ጨምሮ ሌሎችን ጉዳዮች ግንዛቤ መፍጠር፣ ቁጥጥር ማድረግና ተፈጽመው ሲገኙ ለሕግ ማቅረብ ይገኝበታል፡፡ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን መቆጣጠር በስምምነቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በሁለቱ ክልሎች አጎራባች ድንበር አምስት ኪሎ ሜትር መጠነ ዙሪያ ቋሚ የጋራ የጸጥታ ኮሚቴ በማቋቋም የተጠናከረ ፍተሻ ማድረግ በስምምነቱ ትኩረት ከተሰጣባቸው ነጥቦች መካከል ናቸው፡፡ የስምምነቱን አፈጻጸም በየጊዜው ተገናኝቶ መገምግም በስምምነቱ ተካቷል፡፡ ሁለቱ አመራሮች ስምምነቱን ተፈጻሚ ለማድረግ እንደሚሰሩም በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር አረጋግጠዋል፡፡ የክልሎቹ ልዑካን ቡድኖች አባላት ስምምነቱን ካደረጉ በኋላ ችግኞች ተክለዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም