የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለእነ አቶ በረከት ስምኦን የክስ መዝገብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

180
ባህርዳር ኢዜአ ሐምሌ 18/2011 እነ አቶ በረከት ስምኦን በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ከቀረቡ የሰነድ ማስረጃዎች መካከል በእንግሊዘኛ የተጻፉት ተተርጉመው እንዲቀርቡላቸው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርፍድ ቤት የእነ አቶ በረከት ስምኦን መዝገብ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ቀጠሮ የያዘ ቢሆንም ማስረጃዎቹ በሃገሪቱ የስራ ቋንቋ በአማርኛ ያልቀረቡ በመሆናቸው ውሳኔ መስጠት አለመቻሉን አስታውቋል፡፡ ከሰው ምስክር በተጨማሪ ለክስ ማስረጃ ሆነው የቀረቡት የዳሽን ቢራ የሽያጭ ስምምነት ሰነዶች አንዳንዶቹ በእንግሊዘኛ የተጻፉ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ የዳሽን ቢራ የሒሳብ ኦዲትና ዱየት ባሳይ የተባለው ድርጅት  የሽያጭ ውል ስምምነት እንዲሁም ሌሎች ክሱን ያስረዱልኛል ብሎ አቃቤ ህግ ያቀረባቸው ሰነዶች ያልተተረጎሙ በመሆናቸው መርምሮ ብይን ለመስጠት መቸገሩን ችሎቱ አስታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰነዶቹ አልተመረመሩም ውሳኔም አልተሰጠም ሲል ችሎቱ አስረድቷል ፡፡ ተከሳሾች ሰነዶች በእንግሊዘኛ መቅረባቸው ሲመለከቱ አቤቱታ ቢያቀርቡ ኑሮ ከዚህ ቀደም ጎን ለጎን እንዲተረጎም ማድረግ ይቻል እንደበረም ጠቅሷል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ በእንግሊዘኛ የቀረቡት አንዳንድ አስረጅ ሰነዶች ከአማረኛ ትይዩ የቀረቡ በመሆናቸውና ለክርክር አስቸጋሪ አይሆንም በሚል እምነት አንዲቀርቡ ማድረጉን ገልጿል፡፡ የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው  ከሳሽ ጉዳዩን አጣርቶና ጨርሶ ማቅረብ ሲገባው ሳያጠናቅቅ በማቅረብ ደንበኞቼ ለተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እየዳረገ ነው ብለዋል፡፡ አሁንም የቀረበው ሰነድ ተተርጉሞ በአጭር ጊዜ ቀጠሮ እንዲቀርብና ሰነዱ ተመርምሮ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት አቶ በረከት ስምኦን በበኩላቸው እኛ ፖለቲከኞች እንጂ  የህግ ባለሙያዎች ባለመሆናችን የተፈጠረውን ችግር አልተረዳነውም ነበር  ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ አቃቤ ህግ ያስፈለጋል የሚለውን ሰነድ አስተርጉሞ ማቅረብ ሲገባው ባለማድረጉ በእሱ ጥፋት እኛ እየተቀጣን ነው ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ የሁለቱን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ  በአጠቃላይ በእንግሊዘኛ የተፃፉ ሰነዶች የትርጉም ፈቃድ ባለው ህጋዊ አካል በማስተርጎም መሰከረም 22ቀን 2012 ዓ.ም እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾችም በዚሁ ቀን ቀርበው ሰነዱን ተቀብለው በመመርመር ቅሬታ ካላቸው ለመስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም ማቅረብ እንደሚችሉ ጠቅሷል፡፡ ችሎቱ ቀደም ሲል የቀረቡና ተተርጉመው የሚቀርቡ ሰነዶችን በመመርመር መስከረም 30 ቀን 2012 ዓም ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት አጠናቋል፡፡ ይኸው  የሙስና ክስ መዝገብ አቶ በረከት ስምኦን፣ አቶ ታደሰ ካሳና አቶ ዳንኤል ይግዛው ያሉበት ነው፡፡ አቶ ዳንኤል ይግዛው ባለባቸው የጤና እክል ምክንያት ከቀነ ቀጠሮው ቀን በፊት በሃገር ውስጥ ባሉ የህክምና ተቋማት ክትትል እንዲያደርጉም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም