የወረዳው አርሶ አደሮች ለመኸር እርሻ የተለያዩ ምርጥ ዘሮች ባለመቅረባቸው ቅሬታቸውን ገለጹ

1623

ደሴ  ሰኔ 4/2010 ለዘንድሮው የመኸር እርሻ የሚውል የማሽላ፣ ባቄላ፣ ስንዴና ጤፍ ምርጥ ዘር አልቀረበልንም ሲሉ በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ቅሬታቸውን ገለፁ።

በወረዳው ቀበሌ 05 ቀጤ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩት አርሶ አደር ከድር አሊ እንደገለጹት የክረምቱ ወቅት እየመጣ ቢሆንም ለመኽር እርሻ ሥራ የሚያስፈልጋቸውን የባቄላና የጤፍ ምርጥ ዘር እስካሁን እንዳልቀረበላቸው ተናግረዋል፡፡

ምርጥ ዘሩ ፈጥኖ ካልደረሰ ክረምቱ ተጠናክሮ ሲገባ በቀላሉ ለማጓጓዝ ስለሚያስቸግር ተጠቃሚ አንሆንም የሚል ስጋት እንደገባቸው የገለጹት አርሶ አደሩ የዘር ወቅት ሳያልፍ ምርጥ ዘሩ እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል፡፡

በቀበሌ 02 የሚኖሩት አርሶ አደር አሊ ሙሔ  አካባቢያቸው ለማሽላ ምርት ተስማሚ ቢሆንም ምንም ዓይነት ምርጥ ዘር ባለማግኘታቸው የአካባቢ ዝርያ ለመጠቀም መገደዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ምርጥ ዘሩን ለማግኘት ቢጠባበቁም በወቅቱ ምድረስ ባለመቻሉ የአካባቢውን ዘርያ መጠቀማቸውን ጠቁመው ይህም በምርታማነታቸው ላይ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የተሁለደሬ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የግብርና ግብአት አቅርቦትና ስርጭት ቡድን መሪ አቶ ሰይድ አሊ በበኩላቸው ወረዳው ለምርት ዘመኑ 50 ኩንታል የማሽላ፣ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የባቄላና ቦለቄ ምርጥ ዘር ጥያቄ ቢያቅርብም እስካሁን አለመቅረቡን ተናግረዋል::

ከምርጥ ዘሩ በተጨማሪ የዩሪያ ማዳበሪያ አቅርቦቱ ከጥያቄያቸው ጋር የተመጣጠነ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

አንድ ሺህ 474 ኩንታል ዩሪያ ተጠይቆ እስካሁን 859 ኩንታል ብቻ የቀረበላቸው መሆኑን በማሳያነት ገልጸዋል

የምርጥ ዘሩ በወቅቱ አለመድረስም ሆነ የማዳበሪያው አቅርቦት ከፍላጎት ጋር አለመጣጣሙ በምርትና ምርታማነት ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ስለሚችል የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ምርጥ ዘሩ በወቅቱ የማይደርስ ከሆነ ጽህፈት ቤቱ ከአጎራባች ወረዳዎች የተሸለ ምርት የሚያስገኙ የአካባቢ ዝርዎችን በማስመጣት ለአርሶ አደሩ ለማከፋፈል ማቀዱንም አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ ግብርና መምሪያ የግብአት አቅርቦት ባለሙያ አቶ አብርሃም ፀጋዬ በምርት ዘመኑ ለዞኑ የሚያስፈልገው የምርጥ ዘር ኮታ ድልድል ከክልሉ ቢገለጽላቸውም እስካሁን ድረስ ምርጥ ዘሩ በድልድሉ መሰረት እየቀረበ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዘንድሮ የመኸር እርሻ 13 ሺህ 645 ኩንታል ምርጥ ዘር ለዞኑ የሚያስፈልግ ቢሆንም ከክልሉ የተመደበላቸው 9 ሺህ 12 ኩንታል የስንዴ፣ የቢራ ገብስ እና የበቆሎ ምርጥ ዘር ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲቀርብ ከተጠየቀው 146 ሺህ 430 ኩንታል ዩሪያ ውስጥ የደረሰው 69 ሺህ 957 ኩንታል መሆኑን አስታውሰው በጥያቄያቸው መሰረት እንዲሟላ ክትትል በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የክለሉ የግብርና ግብአትና የገጠር ፋይናንስ አቅርቦት  ዳይሬክተር አቶ አለባቸው አሊጋዝ  ዘንድሮ የማሽላና ባቄላ ምርጥ ዘር ጥራቱን ባለመጠበቁ ለአርሶ አደሮች ማቅረብ አለመቻሉን ገልጸዋል።

የስንዴ ምርጥ ዘር በበቂ ሁኔታ ቢኖርም ደቡብ ወሎ ዞን በሰዓቱ አለመውሰዱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ማዳበሪያም በትራንስፖርት ችግር ምክንያት በበቂ ሁኔታ እየደረሰ አለመሆኑንና ችግሩ አገር አቀፍ መሆኑን አስረድተዋል።

በመኸር እርሻው በዞኑ ከሚለማው መሬት 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑም ታውቋል ።