በቤንች ሸኮ ዞን በ”አረንጓዴ አሻራ ቀን” አገር በቀልና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የዕጽዋት ዝርያዎች ይተከላሉ

154

ሚዛን ሐምሌ 16 / 2011 በቤንች ሸኮ ዞን በ”አረንጓዴ አሻራ ቀን” የሚተከሉት ችግኞች አገር በቀልና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የዕጽዋት ዝርያዎች ይሆናሉ።

የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ኃላፊ አቶ በላይ ኮጁዋብ ዛሬ እንዳስታወቁት በዞኑ ሐምሌ 22/2011 በሚደረገው ተከላ  ትኩረቱን አገራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ላላቸው እጽዋት ያደርጋል።

በዕለቱ ለተከላው ሦስት  ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ያስረዱት ኃላፊው፣ከዝርያዎቹ ሰሳ፣ ብርብራ፣ ጽድ፣ ሞሪንጋ፣ ማንጎና አቮካዶን ይገኙበታል ብለዋል።

በዕለቱም  ከ80 ሺህ በላይ ሕዝብ በተከላው እንደሚሳተፍና ከ1 ሺህ 300 በላይ ሄክታር መሬት እንደሚሸፈን  አስታውቀዋል።

ለተከላው የቦታ ልየታና የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን አቶ በላይ ገልጸዋል።

በቤንች ሸኮ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ  አቶ መኳንንት ኃይሉ በበኩላቸው የሚተከሉት ችግኞች ሥነ ምህዳር የሚጠብቁና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።

ችግኞችን ለማጽደቅ ክትትልና እንክብካቤ እንደሚደረግም አመልክተዋል።

ቤንች ሸኮ ዞን በኢትዮጵያ የተሻለ የደን ይዞታ አለባቸው ከሚባሉት አካባቢዎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል።