የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የተቀላጠፈ የመንገደኞችና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ነው

169
ሀምሌ 14/2011 (ኢዜአ) የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የተቀላጠፈ የመንገደኞችና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገለጸ። አክሲዮን ማህበሩ ስራ በጀመረበት የመጀመሪያ አንድ ዓመት ለ150 ሺህ መንገደኞች አገልግሎት መስጠቱ ታውቋል። የትራንስፖርት አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን መቆጠብ እንደቻሉም ገልጸዋል። ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ተጓዡ ሃረን መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የባቡር ትራንስፖርት መጀመሩ በመኪና የሚደረገውን ረጅምና አሰልቺ ጉዞ አስቀርቷል። በወጪ ረገድም ከፍተኛ የሆነ ቅናሽ ያለው በመሆኑ ተጓዦችን ተጠቃሚ እያደረገ ስለመሆኑ ገልጸዋል። ሌላው መንገደኛ ሙሳ አብዲ በበኩላቸው በባቡሩ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲጠቀሙ ለሶስተኛ ጊዜ እንደሆነ ገልጸው፤ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ለሰጣቸው ጥቅም ፕሮጀክቱን እውን ላደረጉት የኢትዮጵያ፣ ጂቡቲና ቻይና መንግስታት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የባቡር ትራንስፖርት ሲገለገሉ የጉዞ ሰነድ አሟልተው በመሆኑም የደህንነት ስጋት እንዳስወገደላቸው ገልጸዋል። የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የባቡር ኦፕሬሽን ቴክኒክ ክፍል ሃላፊ አቶ ዩኑስ ሙሻጋ በለቡ ጣቢያ ውስጥ ባለው የባቡር እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥ የመንገደኞች፣ የጭነትና የጥገና ባቡሮች እንቅስቃሴ ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል። የባቡር መስመር መሰረተ ልማቱ በየጣቢያው ከፍተኛ ቁጥጥር እንደሚደረግበትም እንዲሁ። በግንኙነት መሳሪያዎች አማካኝነት ባቡሮች ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ የመረጃ ልውውጥ እንደሚካሄድም ተናግረዋል። የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ እንደገለጹት፤ የጂቡቲ ተጓዦች አገልግሎት የሚያገኙት ዓለም አቀፍ መስፈርቱን አሟልተው ነው። በቀን እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ መንገደኞች በባቡር ትራንስፖርት እንደሚገለገሉ ጠቁመው ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በ2018 ብቻ 150 ሺህ መንገደኞችን ማጓጓዝ መቻሉን ጠቁመዋል። የባቡር መስመር ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ወደስራ መግባቱ ትልቅ ስኬት እንደሆነ የተናገሩት ኢንጂነር ጥላሁን፤ ''የመንገደኞችንም ሆነ የጭነት የጉዞ ጊዜ በመቀነስ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋዕኦ ትልቅ ስኬት ነው'' ብለዋል። የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር የመንገደኞችና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የጀመረው ታህሳስ 23 ቀን 2010 ዓ.ም መሆኑ ይታወሳል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም