በጋምቤላ ክልል ምክር ቤቶች በቅንጅታዊ አሰራርና ሌሎች ችግሮች ሕዝባዊ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም -አፈጉባዔ ላክደር

76
ጋምቤላ ሐምሌ 16 /2011 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች በቅንጅታዊ አሰራር ጉድለትና ሌሎች ችግሮች ሕዝባዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ አለመሆናቸውን የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ላክደር ላክባክ ገለጹ። የክልሉና የተዋረድ ምክር ቤቶች የጋራ የምክክር መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ  ተጀምሯል። አፈ ጉባዔው አቶ ላከደር  መድረኩን ሲከፍቱ እንደገለጹት በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች በሕገ መንግሥቱ ከሕዝብ የተጣለባቸውን ኃላፊነታቸውን ሲወጡ አይታዩም። ምክር ቤቶቹ የአሰራርና አደረጃጀት ስልጣን የተሰጣቸው የዴሞክራሲ ተቋማት መሆናቸውን ያስታወሱት አፈ ጉባዔው፣በዋነኝነት በቅንጅታዊ አሰራር ጉድለት  የሕዝብ ውክልናቸውንና ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ብለዋል። በተለይም የምክር ቤት አባላት ዕቅዶችን በመድረክ ብቻ ከመገምገም ባለፈ፤ ወደ ወከላቸው ሕዝብ በመዝለቅ የሚነሱ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱ ከአስፈፃሚ አካላት ጋር  በመስራት ክፍተቶች እንደሚታዩ ገልጸዋል። በመሆኑም በአዲሱ በጀት ዓመት የምክር ቤቶች ክፍቶችን በመሙላት እቅዶችን  በመስክ በመገመገምና በመከታተል ጭምር በሕዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች  ምላሽ እንዲያገኙ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። መድረኩ ከአሁን በፊት የነበሩ የአሰራር ችግሮችን ለማስቀረትና በቀጣይ ለሚከናወኑ ሥራዎች መልካም ተሞክሮችን ለመለዋወጥ መዘጋጀቱንም አፈ ጉባዔ ላከደር ተናግረዋል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተንኳይ ጆክ በበኩላቸው ከክልሉ ምክር ቤት በስተቀር በተዋረድ የሚገኙ ምክር ቤቶች በበቂ በጀት ተደግፈው የተጣለባቸውን ኃላፊነት በመወጣት ችግሮች እንዳሉባቸው ገልጸዋል። ስለሆነም ''በአዲሱ በጀት ዓመት በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች የተሰጣቸውን ስልጣንና ተግባር በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል በተሻለ በጀት ልንደግፋቸው ይገባል'' ብለዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው በመድረክ ከክልል እስከ ወረዳ የሚገኙ አፈ- ጉባዔዎችና የክልል፣የዞንና የወረዳ አስተዳሪዎች ተገኝተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም