በባሌ ሮቤ አቅራቢያ አንድ ሚሊዮን 500ሺህ ብር ግምት ያለው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

61
ሀዋሳ ኢዜአ ሐምሌ 16/2011 በባሌ ሮቤ ከተማ አቅራቢያ በተሽከርካሪ ተጭኖ ይጓጓዝ የነበረ አንድ ሚሊዮን 500ሺህ ብር ግምት ያለው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን በኢፌዴሪ ጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ አስታወቀ። በቅርንጫፉ   የውርስ መጋዘን ቡድን አስተባባሪ አቶ ታምሩ ድሪባ ለኢዜአ እንደገለጹት ሐምሌ  /2011ዓ.ም  የተያዙት  የኮንቶሮባንድ እቃዎቹ  በሶማሌ ክልል በኩል ከውጭ ገብቶ  ባሌ ሮቤ ከደረሰ በኋላ  ወደ መሀል ሀገር ለማሳለፍ ሲሞከር ነው። እቃዎቹን ጭኖ ሲያጓጓዝ የተገኘው  ሲኖትራክ የጭነት ተሽከርካሪ ጭምር በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይል በቁጥጥር ስር ውሏል። በተሽከርካሪው ተጭነው ከተገኙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አዳዲስ ልባሽ ጨርቆችና ጫማዎች  ይገኙበታል። ግምቱም አንድ ሚሊዮን 500ሺህ ብር እንደሆነ አቶ ታምሩ አስታውቀዋል። በኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ የባሌ ዞን መምሪያ ባልደረባ  ኮንስታብል ጎሳ አሰፋ በበኩላቸው  የኮንትሮባንድ  እቃዎቹን ጭኖ ሲጓጉዝ ባሌ ሮቤ ከተማ አቅራቢ የተያዘው ተሽከርካሪ ሾፌር ለጊዜው መሰወሩን ገልጸዋል። የኮንትሮባንድ እቃዎቹ ከነተሽከርካሪው የተያዙት  ከአካባቢ ህብረተሰቡ በደረሰ  ጥቆማ መሰረት በተደረገ ክትትል  እንደሆነ ተናግረዋል። እቃዎቹ ለሚመለከተው በኢፌዴሪ  ጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ዛሬ ማስረከባቸውንም አመልክተዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም