ቦሪስ ጆንሰን የዩናይትድ ኪንግደም ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ

74
ኢዜአ ሐምሌ16/2011 ቦሪስ ጆንሰን የወግ አጥባቂ ፓርቲው መሪ ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ ተሰናባቿን ቴሬዛ ሜይን በመተካት ቀጣዩ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ጆንሰን ለወግ አጥባቂ ፓርቲው መሪነት አብረዋቸው የተወዳደሩትን ጀሬሚ ሀንትን በሰፊ የድምፅ ልዩነት አሸንፈዋል። በፓርቲው የድምጽ አሰጣጥ ስርዓት ቦሪስ ጆንሰን 92 ሺህ 153 ድምፅ ሲያገኙ ተቀናቃኛቸው ጀረሚ ሀንት ደግሞ 46 ሺህ 656 ደምፅ ነው ያገኙት። ቦሪስ ጆንሰን በድል ንግግራቸው ጀረሚ ኮርቤይን አሸንፈው የብሪታኒያን ከአውሮፓ ህብረት መነጠልን እውን እንደሚያደርጉ፣ አንድነቷን እንደሚያጠናከሩ ገልጸዋል። በብሬግዚት ፖሊሲያቸው ምክንያት ሥልጣን ለመልቀቅ የተገደዱት ቴሬዛ ሜይ ዛሬ የመጨረሻ የካቢኔ  ስብሰባቸውን ይመራሉ። የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውንም ነገ በይፋ ለንግስት ኤልሳቤት ያቀርባሉ። ቴሬዛ ሜይን የሚተኩት ጠቅላይ ሚንስትር  ቦሪስ ጆንሰን ነገ የንግስቲቷ  መኖሪያ በሆነው  ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት  በሚደረግ ሥነ-ስርዓት ሥልጣኑን  እንደሚረከቡ ቢቢሲ ዘግቧል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም