የደቡብ ክልል የፀጥታ ሥራ በኮማንድ ፖስት መሆኑ ከስጋት አላቆናል---የሐዋሳ ነዋሪዎች

84
ሐዋሳ  ሀምሌ 16/2011 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል የፀጥታ ሥራ በጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት ሥር እንዲቆይ መደረጉ ከስጋት እንዳላቀቃቸው የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። የደቡብ ክልል የፀጥታ ሥራ በጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት ሥር እንዲቆይ መደረጉ ከስጋት እንዳላቀቃቸው የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ ነዋሪዎች እንደተናገሩት በክልሉ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን ተከትሎ በከተማዋ ሰላምና መረጋጋት በመስፈን  ላይ ነው። በዚህም  ተዘግተው የነበሩ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች፣ ባንኮችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ ሥራ ገብተዋል። በከተማዋ በንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ አየነው በልሁ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ በከተማዋና በሲዳማ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች የተከሰተው የፀጥታ ችግር ኮማንድ ፖስቱ  ወደ ሥራ በመግባቱ መቃለሉን ተናግረዋል። ዝርፊያና ድንገተኛ ጥቃትን በመፍራት ሱቃቸውን ዘግተው ለመቀመጥ ተገደው እንደነበር የገለጹት አስተያየት ሰጪው፣መንግሥት ሰላምን ለማስከበር የወሰደው እርምጃ ተገቢ ነው ብለዋል። ወይዘሮ ትሩፋት ዘካሪያስ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ኮማንድ ፖስቱ ሥራ መጀመር የነበረበት ከሐምሌ 11 /2011 አስቀድሞ  መሆን ነበረበት ይላሉ። የከተማዋንና የአካባቢውን ሕዝብ ስጋት ውስጥ የከተተ ጉዳይ መኖሩ እየታወቀ ሕይወት መጥፋትና ንብረት መውደም እንዳልነበረበትም ይናገራሉ። ቢዘገይም በኮማንድ ፖስቱ መቋቋሙ ለሕዝቡ እፎይታ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። በአላሙራ አካባቢ ነዋሪና በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ የተሰማሩት አቶ ውብሸት በላይ የኮማንድ ፖስቱ መቋቋም በሚፈጥረው ሰላምና መረጋጋት በመጠቀም ቤት ንብረታቸው ወድሞባቸው በመጠለያ የሚገኙ ወገኖችን ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የኢዜአ ጋዜጠኛ ዛሬ በከተማዋ ተዘዋውሮ እንዳስተዋለው ከተማዋ ወደ ቀደመው ሕይወቷ መመለስ ጀምራለች።ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መከፈት በተጨማሪ ታክሲና የአገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ሥራ ቀጥለዋል። የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄን ተከትሎ በሐዋሳና በሲዳማ ዞን ወረዳዎች  የተከሰተው የፀጥታ ችግር ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋ በደቡብ ክልል የፀጥታ ሥራ በኮማንድ ፖስት እንዲመራ የተወሰነው ትናንት ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም