ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ንግድን ለማሳለጥ ከተቋቋመው ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያዩ

95
አዲስ አበባ ሐምሌ 16/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ንግድን ለማሳለጥ ከተቋቋመው ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያዩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ስድስት ወራት ንግድን ለማሳለጥ በአገሪቷ የተከናወኑ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችን ከተቋቋመው ኮሚቴ አባላት ጋር የተከናወኑትን ተግባራት በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል። ዛሬ ከኮሜቴው አባላት ጋር በነበራቸው ውይይትም የአገሪቷን የቢዝነስ ዘርፍ እንቅስቃሴ ለማሳደግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይከወናሉ ተብለው የታቀዱ ተግባራትን በመገምገም የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ግቦች ላይ ሊካሄዱ በሚገባቸው ማሻሻያዎች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል። አገሪቷን ለኢንቨስትመንትና ለንግድ ምቹ ለማድረግ የተጀመረው ብሄራዊ የንግድ ማሳለጥ ኮሚቴ አገሪቷ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ፣ ምርታማና በስራ ፈጠራም ሆነ በሌሎች ሥራዎች ስራን በቀላሉ ማከናወን የሚያስችል የአገልግሎት አሰጣጥን ለመዘርጋት እንዲያስችል ዓላማ ያደረገ ኮሚቴ ነው። ኮሚቴው ባለፉት ስድስት ወራት የህግ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው አሰራሮችን በመለየት 8 የሚደርሱ አዋጅና ደንቦች በአዲስ መልክ ተቃኝተው እንዲወጡና ወደ ትግበራ እንዲገቡ ማደረጉም ተገልጿል። ለአብነትም የንግድ ምዝገባና ፍቃድ አዋጅና ተንቀሳቃሽ ንብረትን አስይዞ የብድር አቅርቦት ማግኘት የሚያስችል አዋጅ መጽደቁን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ ተናግረዋል። በተጨማሪም 40 አስተዳደራዊ የህግ ሪፎርሞች መፈፀማቸውን ያብራሩት ኮሚሽነር አበበ፤ ከዚህ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ የንብረት ምዝገባ ፈጣንና የተሳለጠ የማድረግና የግንባታ ፈቃድ አስጣጥን ግልጽነት የመፍጠር ተግባራት መካተታቸውን ተናግረዋል። የህግ ማሻሻያ ሥራዎችን ወደ ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎች የመቀየር ሥራም በመካከለኛ ጊዜ ንግድን ለማሳለጥ ከሚሰሩ ሥራዎች ውስጥ ቀዳሚ መሆኑን አብራርተዋል። ከ60 ዓመት በላይ ያገለገለው የንግድ ህጉ አሁን ከተደረሰበት ዘመን ጋር ተጣጥሞ የብዙ አገራት ምርጥ ተሞክሮዎችን የቀመረ አዲስ የንግድ ህግ ሆኖ እንዲወጣ በቀጣዮቹ አራት ወራት እንደሚወጣም አስታውቀዋል። በአገሪቷ ንግድን በማሳለጥ 3 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች አዳዲስ የሥራ እድል እንዲፈጠር የሚያደርግ ሥራ መሆኑንም ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲፈጠሩ የተፈለገው በርካታ የሥር እድሎች ለዜጎች ተፈጥረው ድህነትን መቀነስ እንዲቻል ነው ብለዋል። ለዚህም ንግድን ለማሳለጥ እየተወሰዱ ካሉ የህግ ማሻሻያዎች ባሻገርም ይህን ተገንዝበው መፈፀም የሚችሉ ተቋማት መፍጠር የግድ ስለሚሆን የተቋማት የሪፎርም ሥራ እንደሚሰራ አመላክተዋል። ባለፈው የካቲት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የንግድ ማሳለጥ መርሃ ግብርን የአንድ ወር የሥራ አፈፃፀም ሁኔታ መገምገማቸው ይታወሳል። በዚህ ወቅት መዋቅራዊ የሥራ አጥነት ችግርን ለመፍታት የግል ዘርፉ ንግድን ለመጀመርና ፋይናንስን በቀላሉ ለማግኘት እንዲችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን መናገራቸው የሚታወስ ነው። ስራን በቀላሉ መከወን የሚያስችል የአገልግሎት አሰጣጥና የህግ ማዕቀፍ ላይ ማሻሻያ እንደሚደረግም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ገልፀው ነበር።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም