ሐምሌ 22 በሚካሄደው አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አሻራችንን ለማኖር ዝግጁ ነን - የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር ሰራተኞች

49
ሀምሌ16/2011 (ኢዜአ)በመጪው ሰኞ ሐምሌ 22 በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግ/ብር አሻራቸውን ለማኖር ዝግጁ መሆናቸውን የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር ሰራተኞች ገለጹ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሰራተኞች ለቀጣዩ ትውልድ በሚተላለፈው ታሪካዊ ስራ አካል በመሆናቸው ደስተኛ መሆናቸውንና ከፍተኛ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። በተደረገው አገራዊ ጥሪ መሰረትም የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንና ችግኝ መትከል በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑንም ነው የገለጹት። ማህበረሰቡ በተለይም ወጣቶች በዚህ ታሪካዊ ስራ ላይ ቢሳተፉ ደግሞ የበለጠ መልካም መሆኑንም የሚኒስቴሩ ሰራተኞች ገልጸዋል። የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንደገለጹት ከ 4 ሺህ በላይ የሚኒስቴሩና የተጠሪ  ተቋማቱ  ሰራተኞች  በአረንጓዴው አሻራ መርሃ ግብር ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ለአገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ እንዲሆኑም ለአጠቃላይ ሰራተኞችና አመራሮች ገለጻ መደረጉንና በዚሁ መሰረት የቁሳቁስ ፣ የትራንስፖርትና ሌሎች ግብዓቶችን የማዘጋጀት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል ።   እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ሚኒስቴሩ ከሌሎች 7 ሚኒስቴሮች ጋር በመሆን በሰሜን ሸዋ ዞን ግራር ጃርሶ ወረዳ ወልጡ በተባለ አካባቢ 50 ሺህ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት አጠናቀዋል። ከችግኝ ተከላው በተጨማሪም በቀጣይነት ለእንክብካቤ ስራዎችም በጀት በመመደብ ለማከናወን መታቀዱንም አቶ ወንድሙ አክለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም