ኢንስቲትዩቱ ሰባት አዳዲስ ዝርያዎች በምርምር አወጣ

56
ባህርዳር ኢዜአ ሐምሌ16/2011 የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በስሩ ከሚገኙ የምርምር ማዕከላት ያወጣቸው ሰባት አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች ለተጠቃሚው መልቀቁን አስታወቀ ። በብሄራዊ ዝርያ አፅዳቂ ኮሚቴ ቀርበው ይሁንታ ያገኙት ዝሪያዎቹ በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የመስጠት አቅም ያላቸው ናቸው ። የኢንስቲትዩቱ የምርምር ህትመት፣ ተግባቦትና የዕውቀት ስራ አመራር ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም ከተለቀቁት አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች መካከል የቢራ ገብስ፣ ማሽላ፣ ዳጉሳ፣ ሁለት የምግብ ሲናርና ሁለት የጤፍ ዝርያዎች ይገኙበታል። በተለይ ሁለቱ የምግብ ሲናር ሰብሎች በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደ ምርምር የተገኙና በሔክታር ከ23 እስከ 38 ነጥብ 6 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ናቸው ። ቃሉ የሚል ስያሜ የተሰጠው የማሽላ ዝርያ በሔክታር 39 ነጥብ 5 ኩንታል፣ የጤፍና የዳጉሳ ዝርያዎቹ እስከ 27 ኩንታል፣ የቢራ ገብስ ደግሞ 24 ነጥብ 6 ኩንታል ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል ። እንደሳቸው ገለጻ ዝርያዎቹ በቀጣይ ዓመት ወደ አርሶ አደሩ በስፋት ሲገቡ የክልሉን የምግብ ዋስትና ክፍተት ለመሙላት እንደሚያግዙና ለውጭ ምንዛሪ ግኝት የሚኖራቸው ድርሻም የጎላ ነው። የሰብል ዝርያዎቹ በአዴትና በስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከላት የተመራማሪዎች ቡድን ያልተቆጠበ ጥረትና ድካም የወጡ መሆናቸውን ገልጸው ዝርያዎቹን ለማውጣት ከሁለት እስከ አምስት ዓመት የወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል። የሰብል ቴክኖሎጂዎቹ ቀደም ሲል በምርምር ተለቀው በአርሶ አደሩ እጅ ከሚገኙ ዝርያዎች ጋር ሲወዳደሩም የተሻለ ምርት መስጠት የሚችሉ ናቸው ተብሏል። በተለይ አሲዳማነትን ተቋቁመው የተሻለ ምርት መስጠት የሚችሉ መሆናቸውን ጠቅሰው ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ እርጥበት ላላቸው አካባቢዎችና ከቆላ እስከ ደጋ ባሉት ስነ-ምህዳሮች ተሞክረው ውጤታማነታቸው ተረጋግጧል ። ግሽበትን፣ የውሃ መቋጠር ችግርንና ድርቅን በመቋቋም ከአካባቢው ዝርያዎች ፈጥነው መድረስ የሚችሉና የሚፈለገውን ንጥረ ነገር ይዘትን ያሟሉ መሆናቸውን አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል። ኢንስቲትዩቱ የክልሉን የዘር አቅርቦት እጥረት ችግር ለመፍታት ታስቦ የሰብል ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ፣ በማስተዋወቅና መነሻ ዘሮችን አባዝቶ የማቅረብ ተልዕኮ ይዞ በ1992 ዓ.ም በክልል ደረጃ የተቋቋመ ነው ። በተቋሙ ስር 14 ዋናና ንዑሳን ማዕከላት ያሉት ሲሆን በስራቸውም ከ40 የሚበልጡ የምርምር ጣቢያዎች እንዳሉት ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም