ከምስራቅ ወለጋ ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀረበው የሰሊጥ ምርት መጠን ቀነሰ

139
ኢዜአ ሀምሌ16/2011በምስራቅ ወለጋ ዞን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለማዕከላዊ ገበያ የቀረበው የሰሊጥ ምርት መጠን ካለፈው ዘመን በሶስት እጥፍ መቀነሱን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ገለፀ ። በጽህፈት ቤቱ የገበያ ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አበበ መገርሳ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ወደ ማዕከላዊ ገበያ የቀረበው የሰሊጥ ምርት 50 ሺህ 460 ኩንታል ነው ። ከዚህ ቀደም ባለው ዓመት ግን 150 ሺህ ኩንታል ሰሊጥ ተመርቶ ለገበያ ቀርቦ እንደነበር አስተባባሪው አስታውሰው "ዘንድሮ ምርቱ አናሳ የሆነበት ዋናው ምክንያት በአካባቢው የነበረው የፀጥታ ችግር ነው" ብለዋል ። በችግሩ ምክንያት በዞኑ በሰሊጥ አምራችነታቸው ከሚታወቁት 13 ወረዳዎች መካከል ከተዘራው የሰሊጥ ሰብል በአግባቡ የተሰበሰበው በሶስት ወረዳዎች ብቻ መሆኑን አስረድተዋል ። በቀሪዎቹ 10 ወረዳዎች ግን ምርቱ ሳይሰበሰብ በማሳ ላይ ረግፎ መቅረቱን ከአቶ አበበ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል። በሳስጋ ወረዳ የሸንኮራ ቀበሌ አርሶ አደር ተካልኝ ረጋሳ ለበርካታ ዓመታት ሰሊጥ በማምረት በሚያገኙት ገቢ የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ለመደጎም ይጠቅማቸው እንደነበር አመልክተዋል። ዘንድሮ ግን በአካባቢያቸው ተከስቶ በነበረው የሰላም መደፍረስ የሰሊጥ ምርታቸውን በማሳ ላይ ረግፎ መቅረቱን ተናግረዋል ። "ችግሩ ለወደፊቱ እንዳይደገም የአካባቢያችን ሰላም ለመጠበቅ የድርሻችን መወጣት አለብን " ብለዋል። ከጤፍና ከሌሎች ምርቶች ይልቅ በትንሽ መሬት ከሚያመርቱት የሰሊጥ ምርት ኑርዋቸውን ለመደጎም እንደሚረዳቸው የተናገሩት ደግሞ በሐሮ ሊሙ ወረዳ የከላላ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ደሳለኝ ሞስሳ ናቸው። በየዓመቱ በአማካይ እስከ 35 ኩንታል ሰሊጥ አምርተው ለገበያ በማቅረብ እስከ 150ሺህ ብር የሚደርስ ገቢ ሲያገኙ እንደነበር ገልፀው ዘንድሮ ግን በሰላም እጦት ምክንያት ባዶ እጃቸው መቅረታቸውን ገልጸዋል። በሰሊጥ ንግድ የተሰማሩት አቶ ከበደ መኮንን በሰጡት አስተያየት በበጀት ዓመቱ በፀጥታ ችግር ምክንያት የንግድ እንቅስቃሴው መዳከሙን ገልፀዋል ። ወጥቶ መግባትና ሰርቶ መክበር የሚቻለው አስተማማኝ ሰላም ሲኖር በመሆኑ ህብረተሰቡ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለሰላሙ መከበር ዘብ መቆም እንዳለበት ጠቁመዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም