የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አንድ ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል በዝግጅት ላይ ነው

110
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 15/2011 በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ አንድ ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ገለጸ። የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አረንዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል። የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ስንታየው ወልደሚካኤል እንደገለጹት፤ የችግኝ ተከላው የሚካሄደው ለሶስት ዓላማ ነው። ኢትዮጵያ ለድርቅ፣ ለጎርፍና ለአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ተጋላጭ እንዳትሆን፣ የባቡር መስመሮች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀልበስና በአገር ግንባታ ሂደት የሚያግባቡ ተግባራት ላይ ኮርፖሬሽኑ የመሳተፍ ማህበራዊ ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ እንደሆነ ገልጸዋል። ለመትከል ከታቀደው 1 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ እስካሁን 100 ሺህ የሚሆኑት የተተከሉ ሲሆን በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ቀሪዎችን ለመትከል እየተሰራ እንደሆነ ዶክተር ስንታየሁ ጠቁመዋል። በተለይም ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ 200 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በተያዘው እቅድ መሰረት ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ 500 ሺህ ችግኞችን እንደሚተክሉ ተናግረዋል። ችግኞችን ከመትከል ባሻገርም ተከታትሎ እንዲጸድቁና ውጤታማ እንዲሆኑም እንክብካቤ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የተቋሙ የአካባቢ ጥበቃ አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ሰመረ በየነ ናቸው። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የጥገና ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ታመነ ሽመልስ በበኩላቸው፤  በሁሉም አካባቢዎች ላይ ችግኞችን በመንከባከብና በመጠበቅ አረንገዴ ኢኮኖሚን ማበልጸግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በዘንድሮው የክረምት ወቅት በገጠር 3 ነጥብ 88 ቢሊዮን በከተማ 760 ሚሊዮን አጠቃላይ 4 ነጥብ 41 ቢሊዮን የዛፍ ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉ ይታወቃል። ተራራማ መልክዓ ምድር የበዛባት ኢትዮጵያ የቀድሞ ደን ሽፋኗ እየተመናመነና አፈሯ እየታጠበ በመሆኑ የደን ሽፋኗን ለመመለስ፣ የዝናብ ስርጭቱን ለማስተካከል፣ የሙቀት ሁኔታውን ለማሻሻል የደን ሽፋን ሁኔታ መለወጥ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት አገራዊ የአረንጓዴ ልማት መርሃ ግብር ወጥቶ እየተሰራ ይገኛል። ኢትዮጵያ ለዓለም አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ካዘጋጁ አገሮች አንዷና የመሪነት ሚናዋን እየተጫወተች ያለች አገር በመሆኗ ከሰባት ቀናት በኋላ በአንድ ቀን 200 ሚሊዮን የዛፍ ችግኝ ለመትከል የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም