”የጉለሌው ጅብ ፈተና ”

171
ገብረህይወት ካህሳይ /ኢዜአ/ በቋሚነት በራሱ ጥረት ጉድጓድ ምሶ የሚኖረው ጅብ ሰው በቆፈረለት ጉድጓድ ውስጥ ዘው ብሎ ገባና መውጫው የሰማይ ያክል ራቀው ። ከ36 ሰዓታት በላይ የነብስ አድን ግብግብ ያካሔደው የጅብ ግልገል ያለሰው ልጆች ድጋፍ ከተዘፈቀበት ጉድጓድ መውጣት ከቶውንም ቢሆን አልተቻለውም ። ጉዳዩ የተከሰተው ሀምሌ 13 ቀን 2011 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ ነው ። ቦታው ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የጉለሌ እፅዋት ማእከል አጠገብ ከሸገር ኤፍኤም ትንሽ ከፍ ይላል ። ለነፍስ አድን ተግባር ወደ እንጦጦ ተራራ ሲጓዝ የነበረው የኢዜአ አንድ ቡድን እግረ መንገዱ የጅብ ግልገሉን ህይወት ታድጎ ተመልሷል ። ቡድኑ ወደ እንጦጦ ያመራው ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓም በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል በተያዘው የአረንጓዴ አሻራ ቀን እቅድ መሰረት የኢዜአ ሰራተኞች ችግኝ የሚተክሉበት ቦታ ለማመቻቸት ነበር ። ዛሬ የምንተክላቸው ችግኞች በዋነኛነት ነገ የኛውኑ ህይወት የሚታደጉ ደኖች መሆናቸውን አያጠራጥርም ። ችግኙ ደን ሆኖ ለዱር እንስሳት መጠለያነት እንደሚያገለግልም ተፈጥሮአዊ እውነታ ነው ። እናም የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ የህይወት አድን ተግባር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ። ቡድኑ ለነብስ አድን ተግባር ተጉዞ የጅብ ግልገሉ ህይወት ታድጎ ተመለሰ ያልነውም ለዚህ ነው ። ብዙም ያልጠነከረው የጅብ ግልገል አገር አማን ነው ብሎ የሌሊት ስራውን ሲያከናውን ዘው ብሎ የገባበት ጉድጓድ ለኤሌክትሪክ ምሰሶ ተብሎ የተቆፈረ ነበር ። ጅቡ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ መሬቱን እየቧጠጠ ለመውጣት ሲታገል ያገኙት ደግሞ የክፍለ ከተማው ሮንዶች ነበሩ ። ታጣቂዎቹ ሓምሌ 14 ቀን ረፋድ 3 ሰዓት አካባቢ ያዩትን ሁሉ ለጉለሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ፅህፈት ቤት ሪፖርት ያቀርባሉ ። የፅህፈት ቤቱ ባለሙያ አቶ ደረጀ ሙሉጌታ አንዴ የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሰባሰብ ጅቡ የሚወጣበት አማራጭ ሲያፈላልጉ መፍትሔው አልመስል ሲላቸው ደግሞ ለዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ለማመልከት ሲያቅማሙ ነበር አምስት አባላት የያዘው የኢዜአ የችግኝ ተከላ አስተባባሪ ቡድን በቦታው የደረሰው ። ክስተቱ አምስቱን አባላት ያስደነቀ ነበር ። ጅቡ ለማውጣት በተደረገው ርብርብ ግን ሶስት ዓይነት ሚና ነበራቸው ። አንደኛው ቡድን ጅቡ እንደምንም መውጣት አለበት የሚል ፅኑ አቋም ይዟል ። ሁለተኛው ቡድን ጎመን በጤና ብሎ ከመጀመሪያው ጥጉን ይዞ አርፎ ተቀምጧል ። ሶስተኛው ቡድን ደግሞ ፈራ ተባ እያለ ቆይቶ ጅቡ ሲንቀሳቀስ እግሬ አውጪኝ ብሎ የፈረጠጠ ነው ። ጅቡ ከነበረበት ጉድጓድ መኪናቸውን እስከ ቆመበት አስፋልት ድረስ የሸሸው  የኢዜአ ባልደረባ በልስቲ  አለምነህ ነበር ። በልስቲ ሮጥክ አሉ ። ይህንን ያክል ፈሪ ነህ እንዴ ? የሚለው የፀኃፊው ቀዳሚ ጥያቄ ነበር ። ” አንተ ራስህ ትቀልዳለህ እንዴ ! ከጅብ ጋር መቃለድን የሚያዋጣው እኮ ሀረር ከተማ ላይ ብቻ ነው ። ምክንያቱን ደግሞ የሀረር ጅቦች ሰው የለመዱ ናቸው ” በሚል መልስ ጠያቂውን መልሶ አፈግጓል ። ጅቡን ከገባበት ጉድጓድ ለማውጣት ሁነኛ መፍትሔ ያገኘው ግን ሾፌሩ ካሳሁን ዓሊ ነው ። ጥረቱ ሰምሮም ጅቡ ከተዘፈቀበት ረግረጋማ ጉድጓድ ወጥቶ ከዘመዶቹ ጋር እንዲቀላቀል አድርጎታል ። ካሳሁን ሒደቱን እንደሚከተለው  ይተርከዋል ። ” ባለማቋረጥ የሚሰቀጥጥ የስቃይ ድምፅ በማሰማትና መሬቱን በመቧጨር ከጉድጓዱ ለመውጣት ይታገላል ። ግን አልቻለም ። አንድ ነገር በማድረግ ልንረዳው እንደሚገባን ተሰማኝ ። መወጣጫ ይሆነው ዘንድም ጉቶ ነገር ወደ ጉድጓዱ ጨመርኩኝ ። አሁንም አልቻለም ። እናም ረዘም ያለ ተጨማሪ እንጨት አስገባንና ተንጠላጥሎ ወጣ ” ይለናል ። ጅቡ እንደ ምንም ከወጣ በኋላ ወደ ሰዎች ዞር ብሎ ሳይመለከት ባለ በሌለ አቅሙ ፍጥነቱን ጨምሮ ወደ ጫካ መፈትለኩን ሾፌሩ ካሳሁን ዓሊ በፈፀመው ተግባር መርካቱን በሚያንፀባርቅ መልኩ ተናግሯል ። ሾፌሩ ካሳሁንና አቶ ደረጀ ጅቡን ለማውጣት ሲታገሉ ሌላው የኢዜአ ባልደረባ አቶ ዮሃንስ ወንድይራድ ደግሞ በቪዲዮ በመቅረፅና ፎቶ ግራፍ በማንሳት ክስተቱን ለታሪክ በተንቀሳቃሽ ስልኩ አስቀርቶታል ። ይህንን ክስተት ለመፃፍ ያነሳሳኝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እየታየ የመጣውን የእርስ በርስ ግጭት መነሻ በማድረግ ነው ።ግጭቱ አሁንም ድረስ እንቆቅልሽ እንደሆነብኝ ነው ። በአንድ በኩል ኢትዮጵያዊ ባህላቸውን ጠብቀው በአምሳላቸው ለተፈጠረው የሰው ልጅ ይቅርና ለእንስሳትም ጭምር የሚያዝኑና የሚሳሱ ደጎችና ርህሩሆች ያሉባት ምድር ናት -ኢትየጵያ ። በሌላ በኩል ደግሞ ወንድም በወንድሙ ላይ እየተነሳ በጠራራ ፀሃይ የመንጋ ጥቃት ሲፈፅም ይታያል ። ታዲያ ! እነዚህ በአንድ ሚዛን እኩል ማስቀመጥ ይቻል ይሆን የሚለውን ጥያቄ በመሰንዘር እንድንነጋገርበት ለመነሻ ያክል  ነው። ነገርን ነገር ያነሳዋል ይባል የለ ? ስለ ጅብ ሲነሳ የአዲስ አበባ ከተማና የጅቦች ገጠመኞችን አስመልክተው የኢዜአ ባልደረቦቼ የሚከተሉትን ሓሳቦች አካፍለውኛል ። ”በአስኮ ሊዝ ሰፋር አንድ ጅብ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበቴ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ሲቁለጨለጭ ተገኘ” ያለኝ ባልደረባዬ መታፈሪያ ግርማ ነው ። ሌላዋ የስራ አጋሬ የንጉስ ውቤ በበኩላ በቅርቡ አንድ ጅብ ቦሌ አራብሳ ኮንደሚኒየም 4ኛ ፎቅ ላይ ተገኝቷል ። በልስቲ አለምነህ የሰማውን እንዳጋራኝ ከሆነ ደግሞ ጅቦች አዲስ አበባ መኸል ከተማ ድረስ እንደሚዘልቁ ነው ። ባሻ ወልዴና ሰሚት ኮንዶሚኒየሞች አካባቢ ጎራ ማለታቸው የተለመደ ነው ብሏል ። ጅቦቹ ከተማ ያስመረጣቸው  በእኛው በሰው ልጆች ጦስ መጠለያቸውን መንጥረን በቂ ምግብ እንዳያገኙና መረጋጋት እንዲያጡ በማድረጋችን ነው ። ግድ የለም ! ጦሰኞቹ እኛው ብንሆንም ልንክሳቸው ደግሞ እሽር ጉድ ማለት ጀምረናል ። ችግኞችን በመትከል ለእኛም ሆነ ለእነሱ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ። ስለዚህ ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ፍጥረታት ህልውና አረንጓዴ ልማት መከተል አማራጭ ሳይሆን ተመራጭ ነው ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም