ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከፈረንሳይ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

213

አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ15/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፈረንሳይ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር እና ከአውሮፓ ህብረት ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኮሚሽነር ጋር ተወያዩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ የአንድ ቀን ጉብኝት በማድረግ ላይ ከሚገኙት  የፈረንሳይ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ብሩኖ ሊ ሜር ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

እያደገ የመጣውን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መነጋገራቸውን  የፈረንሳይ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቀጣናው ይዘው የመጡት አዲስ ሀሳብና  የለውጥ ፕሮግራም ውጥን እንዲሳካ ሙሉ ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀው ይህንኑ ድጋፍ ፈረንሳይ እንደምታጠናክር ብሩኖ ሊ ሜር አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከሚባሉ አገራት መካከል መሆኗን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ቢዝነስን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየወሰደች ያለውን የማሻሻያ እርምጃ አድንቀዋል።

የፈረንሳይ ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት መዳረሻቸው ኢትዮጵያ እንደምትሆን ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በቀጣይ በትብብር የሚሰሩባቸው ናቸው ያሏቸውን ዘርፎችም አንስተዋል።

ከውይይታቸው በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር በመሆን በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ቅጥር ግቢ  ችግኝ ተክለዋል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከአውሮፓ ህብረት ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኮሚሽነር ኔቨን ሚሚካ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው የለውጥ ሂደት የአውሮፓ ህብረት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንደገለጹላቸው ኮሚሽነር ኔቨን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።