ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለፀች

62
አዲስ አበባ ሐምሌ15/2011 ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነትና የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የአገሪቱ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ገለፁ። የፈረንሳይ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ብሩኖ ሊ ሜር በኢትዮጵያ የአንድ ቀን ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ከነልዑካቸው ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል። በውሏቸውም ከገንዘብ ሚኒስቴር አመራሮች ጋር የተወያዩ ሲሆን ሁለቱ አገራት በተለይ በኢነርጂና ሎጅስቲክ ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት ለማጎልበት ተስማምተዋል። የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ስለሁለቱ አገራት ግንኙነት መጠናከር መወያየታቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ የእርሳቸው አዲስ አበባ መምጣትም ግንኙነቱን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልፀዋል። ሁለቱ አገራት በተለያዩ ዘርፎች የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ያላቸው ሲሆን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ስለሚከወኑ ፕሮጀክቶች በዛሬው ዕለት መወያየታቸው ይታወቃል።  በሌሎችም መስኮች መሰል ትብብሮች እንደሚደረጉም ተናግረዋል። አገራቸው በተለይ በኢነርጂና በሎጅስቲክ ዘርፍ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቷን ገልፀው በቅርቡ በኢትዮጵያ ለዲጂታል መታወቂያ መርሃ-ግብር የሚውል የ40 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጅት እያደረገች ነው ብለዋል። ከፈረንሳይ ልዑካን ጋር በተደረገው የሁለትዮሽ ውይይት በሁለቱ አገራት ትብብር የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ ውይይት መደረጉንና በቀጣይ የአገራቱን ግንኙነት ለማጠንከር የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ናቸው። ፈረንሳይ የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር ከመሆኗ በተጨማሪ የአገሪቱን ሁሉን አቀፍ ለውጥ እየደገፈች ያለች መሆኗን አስረድተው የተደረገው ውይይት የሁለትዮሽ ግንኙነትን ከማጠንከር በተጨማሪ የንግዱ ማህበረሰብ እየገጠመው ያለውን ችግር መፍታት የሚያስችል ውይይት የተደረገበት እንደሆነም ገልፀዋል። አገሪቱ በቀጥታ ከምታደርገው ድጋፍ ባሻገር በዓለም አቀፍ የልማት ተቋማት ለኢትዮጵያ የምታደርገውን እገዛም አድንቀዋል። የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠንከር እንዲህ አይነት ውይይቶች እንደሚቀጥሉም ነው ያስረዱት ሚኒስትሩ። በውይይቱ አገራቱ በኢነርጂ፣ በሎጅስቲክና በቴሌኮምና በሌሎችም ዘርፎች የሚኖራቸው ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም