የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህላቸው ለማድረግ እንጥራለን አሉ

57
ሐረር ሐምሌ 15 / 2011 የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህላቸው ለማድረግ እንደሚሰሩ የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች ተናገሩ። ነዋሪዎቹ  መርሃ ግብሩን ለማስጀመር  በተዘጋጀው መድረክ ላይ እንደገለጹት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነትን የሚያሳድገውን አገልግሎት ልምድ አድርገው ይቀጥላሉ። ከአስተያየት ሰጪዎቹ ወይዘሮ አመዘነች ታምራት በተበታተኑ መንገዶች ሲሰጥ የነበረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተቀናጀና ወጥ በሆነ መንገድ እናከናወናለን ያሉት ይህንንም ለማሳከት ከኅብረተሰቡ ጋር ሆነን ወደ ስራ ገብተናል ብለዋል ። ለአገራችንና ለማህበረሰቡ የምናደርገው ግዴታ በመሆኑ አገልግሎቱ ደስተኛ አድርጎኛል የሚለው ወጣት መሃዲ ኢብሮሽ ፣ ሥራውን ለተሻለ የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲውል የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ ሲል ተናግሯል። በተለይ በሰላምና ጸጥታ ስራ ላይ የተቀናጀ ስራ እናከናውናለንም ብሏል። ከዚህ ቀደም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአንድ ሰሞን ስራ ሆነው ሲስተዋሉ አይቻለሁ ያለው ወጣቱ ፣ አሁንም ይህ ሁኔታ እንዳይታይ መንግሥት ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል። የአገር ሽማግሌው አቶ አብራሂም ኡመሬ በበኩላቸው አገልግሎት ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የአገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባቸውን ለማድረግና ኅብረተሰቡንና ወጣቱን ለማነሳሳትና ለማገዝ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። የኦሮሚያ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ ለውጡን ለማስቀጠል የሚቻለው ሁሉም በተሰማራበት ውጤታማ ስራ ሲያከናውን በመሆኑ ሁሉም የዜግነት ድርሻውን ሊያበረክት ይገባል ብለዋል። በአካባቢ ልማት፣ሰላምና ጸጥታ ዙርያ የሚሰሩ ስራዎችን በዚህ ዘመን በሚመጥኑ መልኩ በማውረድ መተግበር ይገባል፤ለዚህም በመንግሥት በኩል ቁርጠኝነት እንዳለ ተናግረዋል። የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አባድር አሚኖ አገልግሎቱ መታወጁ ዜጎች ለአገራቸው የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል። በዞኑ በአገልግሎቱ 100 ሚሊዮን ችግኝ ይተከላል የደም ልገሳ፣የአረጋውያን ቤቶች ማደስ፣የአካባቢ ጽዳትና ሌሎች የበጎ አድራጎት ስራዎች ይከናወናሉ። በአገልግሎቱ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የዞንና የወረዳ አመራር አካላት፣የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ወጣቶችና ሴቶች የተገኙ ሲሆን፣ የደም ልገሳና የችግኝ ተከላ ተግባራት ተከናውነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም