ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ የአቪዬሽን ዘርፍ ስኬት ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች

69
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 15/2011 የፈረንሳይ መንግስት በኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ስኬታማነት ድጋፍ እንደሚያደርግ የአገሪቱ የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ገለጹ። በኢትዮጵያ የአንድ ቀን የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ የገቡት ብሩኖ ሊሜር ከልዑካናቸው ጋር በመሆን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ጋር የአቪዬሽንን ዘርፍ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። የፈረንሳይ ኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ብሩኖ ሊሜር እንደገለጹት አገራቸው በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ዘርፍ ድጋፍ እያደረገች ያለችባቸው ፕሮጀክቶች ግንባታ እንዲፋጠኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች። ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደምትፈልግና ለዚህም ትብብር መጠናከር የአየር መንገዱ ሚና ቁልፍ እንደሆነ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማ እንደሆነና የፈረንሳይ ኩባንያዎች ከአየር መንገዱ ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ በማድረግ አየር መንገዱን የሚያከናውናቸውን የፈረንሳይ መንግስት መደገፍ እንደሚፈልግ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከአየር መንገዱ ጋር የሚሰሩ የፈረንሳይ ድርጅቶች ግንኙነታቸውን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል። በውይይቱ ወቅት ከኤር ባስ አውሮፕላኖች ግዢ ጋር ውይይት እንደተደረገና አየር መንገዱ ኤር ባስ የሚያመርታቸውን ሌሎች የአውሮፕላን አይነቶች እንዲገዛ ከሚኒስትሩ ሀሳብ እንደቀረበም ጠቅሰዋል። አየር መንገዱ ከፈረንሳዩ ኩባንያ ሳፍራን የቦይንግ 737 አውሮፕላኖች ሞተር እንደሚገዛና የአውሮፕላን ሞተሮችን ጨምሮ የጥገና ስራዎችን አየር መንገዱ እንደሚያከናውን ገልጸው በዚህ ረገድ ከኩባንያው ጋር ያለውን ግንኙነት ማስፋት ላይ ውይይት ተደርጓል ብለዋል። የአማካሪ ድርጅት የሆነው የፈረንሳዩ ኤርፖርት ዲ ፓሪ ኢንተርናሽናል ኩባንያ በአዲሱ አየር ማረፊያ ግንባታ የቦታ መረጣ ላይ እንደተሳተፈና በቀጣይ ተወዳድሮ በአየር ማረፊያ ግንባታ ላይ በአማካሪነቱ ስራ ሊቀጥል እንደሚችልም አመልክተዋል። በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ላይ ላጋርድን ጨምሮ ሌሎች ከቀረጥ ነጻ ዕቃ ሻጭ የፈረንሳይ ድርጅቶች ለዓለም አቀፍ ተጓዦች አገልግሎታቸውን እንዲያሰፉ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን ገልጸዋል። አጃንስ ፍራንስ ዴቨሎፕመንት ተብሎ የሚጠራው የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ የአየር መንገዱ ዋንኛ አጋር እንደሆነና ለአቪዬሽን አካዳሚው ግንባታና ለካርጎ ተርሚናል እንዲሁም ለአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ የብድር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በክልል ለሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች ማስፋፊያ የልማት ኤጀንሲው 100 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ብድር ማዘጋጀቱንና ብድሩን መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደጀመረም ነው አቶ ተወልደ የሚገልጹት። በኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ የሚመረቁ ተማሪዎች የሚያመርቷቸውን ዕቃዎች ለፈረንሳይ የአቪዬሽን ተቋማት እንዲያቀርቡ አየር መንገዱ ግፊት እያደረገም ነው ብለዋል። በውይይቱ ወቅት አየር መንገዱ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በገነባቸውና ወደፊት በሚገነባቸው የመተላለፊያ ማዕከላት ላይ ከፈረንሳይ ኩባንያዎች ጋር በትብብር እንዲሰራና የማዕከላቱን አቅም ለመገንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት መደረጉንም አክለዋል። ሚኒስትሩ ብሩኖ ሊሜር በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ከገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ጋር የአገራቱን ግንኙነት ይበልጥ በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሏል። ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁም ወደ ኬኒያ እንደሚያመሩ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም