የአማራ ምክር ቤት ጉባኤ ተጀመረ

48
ባህር ዳር (ኢዜአ) ሐምሌ 15 / 2011 የአማራ ክልል ምክር ቤት አምስተኛ ዙር፣ አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባኤ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተጀመረ። ምክር ቤቱ በመጀመሪያ አጀንዳው የአማራ ዴሞክራሲ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት እንዲመሩ በዕጩነት ያቀረባቸውን የአቶ ተመስገን ጥሩነህን ሹመት ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል። የርዕሰ መስተዳደሩ ሹመት በምክር ቤቱ ከፀደቀ በኋላ ቃለ መሀላ ፈጽመው ለጉባኤተኛውና ለክልሉ ህዝብ መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ከወጣው መርሀ ግብር ለመረዳት ተችሏል ። ጉባኤው ከዛሬ ሐምሌ 15 ቀን 2011  ጀምሮ ለሚቀጥሉት 4 ቀናት በሚኖረው ቆይታ የ2011  የክልሉ የአስፈፃሚ አካላት የ11 ወራት ክንውን የተጠቃለለ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል። እንዲሁም የክልሉን ዋና ኦዲተርና የጠቅላይ ፍርድ ቤት መስሪያ ቤቶችን ሪፖርትም የሚያዳምጥ ሲሆን በቆይታውም የክልሉን የ2012  በጀት መርምሮ እንደሚያጸድቅ ታውቋል። በመጨረሻም ምክር ቤቱ ልዩ ልዩ ሹመቶችን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም