የአሶሳ እና ወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች የወዳጅነት እግር ኳስ ውድድር አካሄዱ

64
አሶሳ ኢዜአ ሐምሌ 14 / 2011  የአሶሳ እና ወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር ዓላማው ያደረገ የወዳጅነት እግር ኳስ ውድድር አካሄዱ። የዩኒቨርሲቲዎቹ መምህራንና እና አስተዳደር ሠራተኞች በተሳተፉበት የተካሄደው ውድድር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልሎች መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑም ተገልጿል። ዛሬ በአሶሳ ከተማ ወጣቶች ማዕከል በተካሄደ በእዚህ ውድድር አሶሳ ዩኒቨርሲቲ የወለጋ ዩኒቨርሲቲን 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ናሆም ጀምስ ለኢዜአ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲዎቹ ያደረጉት ስፖርታዊ ውድድር ሃገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ነው፡፡ “አሶሳ ዩኒቨርሲቲ በርካታ መልካም ተሞክሮዎችን ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ መቅሰም ይፈልጋል” ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ በዩኒቨርሲቲዎቹ መካከል የማህበረሰብ አገልግሎት ስምምነት ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል። የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ገልጸው “ውድድሩ የክልሎቹ ህዝቦች አብሮነታቸውን ለማስቀጠል እንደሚፈልጉ አንድ ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ቡድን ተወካይ አቶ ሚልኬሳ ጉርሜሳ ዩኒቨርሲቲዎቹ በስፖርቱ የጀመሩትን አንድነት የህብረተሰቡን ችግሮች በሚፈቱ ጉዳዮች ላይ ቢያጠናክሩ ውጤታማ ይሆናሉ ብለዋል፡፡ በውድድሩ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ሚልኪያስ “የውድድሩን ዓላማ በማሳካታችን ደስተኞች ነን" ሲሉ ተናግረዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም