አድማስ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 7 ሺህ ተማሪዎች አስመረቀ

115
ሐምሌ 14 /2011ዓ.ም  (ኢዜአ)አድማስ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 7 ሺህ ተማሪዎች በዛሬው እለት አስመረቀ። ዩኒቨርስቲው በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በተከናወነ ስነ-ስርዓት ያስመረቃቸው ተማሪዎች በዲግሪና ዲፕሎማ በመደበኛና ተከታታይ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ናቸው። በዚህ ጊዜ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሞላ ፀጋይ እንደገለጹት ዩንቨርስቲው በአገሪቷ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት በምታደርገው ጥረት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል። ዩኒቨርስቲው እያደረገ ያለውን የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንቱ አክለዋል። አድማስ ዩኒቨርስቲ ባለፉት 20 ዓመታት በመደበኛና በርቀት መርሃ ግብሮች በዲግሪ፣ ዲፕሎማና በሰርተፊኬት ከ60 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል። በአሁኑ ወቅትም በውጭ ሶማሌላንድና ፑንትላንድ በሚገኙት ካምፓሶቹ ያሉትን ጨምሮ በጠቅላላው ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም