ህዝቡ ሰላሙን ለመጠበቅ እያደረገ ያለው ጥረት በክልሉ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እያገዘ ነው…ዶክተር ደብረፅዮን

359

መቐለ ሐምሌ 14 / 2011  የትግራይ ህዝብና የክልሉ መንግስት ከፀረ ድህነት ትግል በተጨማሪ የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለመጠበቅ እያደረገ ያለው ጥረት በክልሉ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እያገዘ መሆኑ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ::

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ይህን ያሉት የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ዛሬ በጀመሩት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ነው።

በእዚህ ወቅት ዶክተር ደብረፅዮን እንዳሉት በተያዘው ዓመት የክልሉን ሰላም የሚፈታተኑ በርካታ እንቅፋቶች ቢኖሩም በህዝቡና በክልሉ መንግስት በሳል አመራር ምንም ችግር ሳይፈጠር መቆየቱን ተናግረዋል።

“አሁንም ከድህነት በላይ ዋነኛ ጠላት የለንም” ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ከዚህ በላይ አጀንዳ እንደሌላቸው ነው የገለጹት።

በክልሉ ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በተሰሩ በርካታ ሥራዎች በክልሉ ኢንቨስትመንት እየተስፋፋ መምጣቱን ዶክተር ደብረፅዮን አስረድተዋል።

መሰረተ ልማት ሥራዎችን ከመዘርጋት ጎን ለጎን ስራአጥነትን ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ ያለበትን የበጀት እጥረት ለመቅረፍ ባለሃብቶች የጀመሩትን ጥረት አድንቀዋል።

ባለሃብቱ፣ ህዝብና መንግስት ተደጋግፈው በክልሉ ያሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት ቀጣይነት ያለው ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም ዶክተር ደብረፅዮን አሳስበዋል።

የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ኃይሉ በበኩላቸው ’’ በክልሉ ድህነትና የሥራ እጥነት ሳይቀረፍ ለብቻው የሚንቀሳቀስ ባለሃብት በዘላቂነት እድገት አያመጣም።’’ ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ያጋጠመውን የበጀት እጥረት ለመቅረፍ የንግዱ ማህበረሰብ የበኩሉን እንዲያበረክት በማሰብ የገቢ ማሰባሰብ መርሀ ግበር መዘጋጀቱንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ዛሬ ከሰዓት በኋላ በመቀለ ሰማዕታት ኃውልት በተጀመረው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ላይ እስከ 250 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ የታቀደ ሲሆን መርሀ ግብሩ በተጀመረ በ15 ደቂቃ ውስጥ 84 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ተችሏል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።