ፋሲል ከነማ የኢትዮጵያ የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ ሆነ

143
ሐምሌ 14 / 2011ዓ.ም  (ኢዜአ)  ፋሲል ከነማ የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ ሆነ ዛሬ በቢሾፍቱ ሜዳ በተካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ተጋጣሚውን ሀዋሳ ከተማን በመለያ ምት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ ሆኗል። መስፍን ታፈሰ ከእረፍት በፊት ባስቆጠረው ግብ ሀዋሳ ከተማ መሪ ቢሆን ቢችልም ከእረፍት መልስ የፋሲል ከነማው አምበል ያሬድ ባዬ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠረው ግብ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጨዋታው 1 ለ 1 በሆነ ውጤት በመጠናቀቁ ሁለቱ ክለቦች ቀጥታ ወደመለያ ምት ያመሩ ሲሆን በመለያ ምቱ ፋሲል ከነማ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የጥሎ ማለፍ ዋንጫው ባለቤት ሆኗል። ፋሲል ከነማ የውድድሩ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ይሳተፋል። ከታህሳስ ወር 2011 ዓ. ጀምሮ በተዘበራረቀ እና ባልተቀናጀ መልኩ የተካሄደው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ውድድር የፎርፌ ውጤቶች የውድድሩ ዋንኛ መገለጫ ነበሩ ማለት ይቻላል። ከፕሪሚየር ሊጉ 14 ክለቦች መካከል ስምንቱ በአብዛኛው ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ ችግር በተለያየ ወቅት ከውድድሩ ራሳቸውን አግለዋል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መቐለ ሰብዓ እንደርታ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረ፣ ደደቢት፣ ጅማ አባ ጅፋር እና አዳማ ከተማ ራሳቸውን ከውድድሩ ያገለሉ ክለቦች ናቸው። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከውድድሩ ራሳቸውን በማግለላቸው ከጥሎ ማለፍ ውድድሩ መካከል ስምንት ጨዋታዎች በፎርፌ ውጤት የተጠናቀቁ ሲሆን ክለቦች እርስ በእርስ ተጫውተው የተሸናነፉባቸው ጨዋታዎች ብዛት ደግሞ ሰባት ብቻ ነው። ፋሲል ከነማና ሀዋሳ ከተማ ለፍጻሜ ያለፉት በቅደም ተከተል መቐለ ሰብዓ እንደርታንና ኢትዮጵያ ቡናን በፎርፌ ውጤት አሸንፈው ነው። በአጠቃላይ የፎርፌ ውጤቶች ሜዳ ላይ ከተካሄዱ ጨዋታዎች በልጦ በታየበት የዘንድሮው የኢትዮጵያ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር ክለቦች ፉክክር አድርገው ተጠናቀቀ ለማለት በማያስችል መልኩ ዛሬ በቢሾፍቱ ሜዳ ፍጻሜውን አግኝቷል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም