በአማራ ክልል 37 ሚሊዮን 800ሺህ ብር ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

227

ሐምሌ 13/2011(ኢዜአ)  በአማራ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 37 ሚሊዮን 800ሺህ ብር ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የባህርዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ከውጪ ሊገቡ ሲሉ ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል 12 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው 29 ሺህ 774 የጦር መሳሪያዎች ይገኙበታል ።

የጽህፈት ቤቱ የህግ ተገዥነት ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ተስፋ አራጋው ለኢዜአ እንደገለጹት   የኮንትሮ ባንድ ዕቃዎቹ የተያዙት በህገ ወጥ መንገድ ወደሀገር ውስጥ ሲገቡና ወደውጭ ሊወጡ ሲሉ በተደረገ ድንገተኛና መደበኛ ፍተሻ ነው።

በመደበኛ የፍተሻ ጣቢያዎች ከሚደረገው የክትትልና ቁጥጥር ስራ በተጨማሪ በተለያየ ጊዜያት በተደረጉ ድንገተኛ ፍተሻዎች፣ በደፈጣና በፓትሮል የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ መያዝ ተችሏል።

ከውጭ ወደሀገር ውስጥ ሲገቡ ከተያዙ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው 29 ሺህ 774 ክላሽና ሽጉጦች፣ እንዲሁም የተለያዩ የጦር መሳሪያ ጥይቶች ተጠቅሰዋል።

አዳዲስ አልባሳት ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የሲጋራና ትንባሆ ምርቶች፣ የተለያዩ መድኃኒቶች፣ አደንዛዥ ዕፆች፣ ምግብ ነክና የታሸጉ ለስላሳ መጠጦች ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መካከል ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ገንዘብን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች፣ የከበሩ ማዕድናት፣ የቁም እንስሳት፣ የባህል ጫማዎችና ሌሎች ዕቃዎች በሱዳን አቅጣጫ ሊወጡ ሲሉ ተይዘዋል ።

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በህብረተሰቡ ጥቆማ ፣ በተቋሙ ኢንተለጀንስ ባለሙያዎች፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች፣ በመከላከያ ሰራዊትና በአጋር አካላት ቅንጅት ክትትልና ቁጥጥር የተያዙ ናቸው ተብሏል ።

የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ጭነው ሲያጓጉዙ ከተገኙ 148 ተሽከርካሪዎች መካከል አስፈላጊውን የማጣራት ስራ በማካሔድ 23 ተሽከርካሪዎች እንዲወረሱ ተደርጓል ።

የሁለት ተሽከርካሪ ባለቤቶች ለዋናው መስሪያ ቤት አቤቱታ አቅርበው ጉዳያቸው እየታየ ሲሆን የ18 ተሽከርካሪዎች ጉዳይ ደግሞ ደግሞ በቅርንጫፉ እየተጣራ ይገኛል።

ቀሪዎቹ ተሽከርካሪዎች በቅርጫፍ ጽህፈት ቤቱና በመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ጉዳያቸው ተጣርቶ በማስጠንቀቂያና በነፃ መለቀቃቸውን አቶ ተስፋ አስረድተዋል።

ኮንትሮ ባንድን ለመከላከል በበጀት ዓመቱ በተደረገው ጥረትም የተያዙ ዕቃዎች ግምት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል።

በ2010 በጀት ዓመት ቅርንጫፍ ጽህፈት 26 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት ያላቸው የኮንትሮ ባንድ ዕቃዎች ተይዞ ነበር ።