የሶማሌና የአማራ ክልል ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ መድረክ እየተካሄደ ነው

157

ባህር ዳር ኢዜአ ሐምሌ 14 / 2011- የሶማሌና የአማራ ክልል ህዝቦች የጋራ የህዝብ ለህዝብ መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ የአማራ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌው እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በነበረ የተሳሳተ ትርክት የአማራ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች እንዲገለል ሲሰራ ቆይቷል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕስመስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ በክልሉ ከተለያየ የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ የልኡካን ቡድንን ይዘው ወደ አማራ ክልል በመምጣታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውም ተናግረዋል።

የህዝብ ለህዝብ መድረኩ በአማራ ህዝብ ላይ ሲነዛ የነበረውን የተዛባ ትርክት ለማስተካከልና እውነታውን ለሁሉም ህብረተሰብ በአግባቡ ለማሳወቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ገለፀዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ህዝቦች የቀደመ አንድነታቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳሩ አክለው እንዳሉት የአማራ ህዝብ ያለስራው ስም እንደተሰጠው ገዢና ጨቋኝ ሳይሆን ከራሱ በላይ ለሀገሩና ለኢትዮጵያ አንድነት የሚጨነቅ ህዝብ ነው።

ኢትዮጵያ ከገጠማት የፖለቲካ ችግር ፈጥና እንድትወጣ ዛሬም እንደትናንቱ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር ግንባር ቀደም በመሆን ከፍተኛ ትግል እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአማራ ህዝብ ከወንድም የሶማሌ ህዝብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለውና በካራማራ ተካሄዶ በነበረው ጦርነትም ኢትዮጵያን በጠላት ላለማስደፈር በተደረገ የጋራ ተጋድሎ በአንድ ጉድጓድ የተዋደቀ ህዝብ መሆኑንም አቶ ላቀ አስታውሰዋል።

ይህንን የቆየ የኋላ ታሪክ የተረዳው የሶማሌ ክልል ህዝብና መንግስት ቀድሞ የነበረው ወንድማማችነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየሰራ ያለውን ስራ በማመስገን የአማራ ክልል ህዝብና መንግስትም ከክልሉ ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን አስረድተዋል።

እንደአቶ ላቀ ገለጻ፣ አሁን ኢትዮጵያ ከተደቀነባት ችግር ፈጥና እንድትወጣ የሶማሌና የአማራ ክልል መንግስታት የማዕከላዊ መንግስትን በማጠናከር በኩል በጋራ እየሰሩ ነው።

በአማራና ሶማሌ ክልሎች መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ከሶማሌ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጠጡ 100 የሚሆኑ የሉዐካን ቡድን አባላት ወደ ባህር ዳር ከተማ ከገቡ ዛሬ ሦስተኛ ቀን መያዙ ይታወቃል።