ተደራጅተው በተማሩት ሙያ ለመሰማራት መዘጋጃታቸውን በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ

161

መቀሌ ኢዜአ ሐምሌ 13/2011 ተደራጅተው በተማሩት ሙያ ሰራ ፈጥረው ለመሰማራት ዝግጁ መሆናቸውን በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የዛሬ ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ።

ከተመራቂዎቹ መካከል በሲቪል ምህንድስና ሙያ የተማረው  አስቻለው ደምስ በሰጠው አስተያየት  በዩኒቨርስቲ ቆይዬ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመጡ ተማሪዎች ጋር  በመተዋወቅ ተቻችለው በፍቅር ማሳለፋቸውን ተናግሯል።

“ከመንግስት ስራ ከመጠበቅ አብረውኝ ከተመረቁ የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ጋር በማህበር ተደራጅተን በሙያችን የራሳችን ስራ በመፍጠር ለመንቀሳቀስ ተዘጋጅተናል”  ብሏል።

በምጣኔ ሀብት ሙያ የተመረቀችው ኤደን ኃይለማሪያም በበኩሏ  “ከዩኒቨስቲ የተማርኩት ትልቁ ነገር ከተለያዩ የሀገራችን ክልሎች የመጣን ተማሪዎች ተቻችለንና ተከባብረን አንድነታችን አጠናክረን በመማራችን ነው ” ብላለች።

በዩኒቨርስቲ ቆይታዋ ያገኘችውን  የህይወት ተሞክሮ የቀሰመችው ሙያ  በምትሰማራበት  የስራ መስክ ሁሉ ከጓደኞቿ ጋር ተደራጅታ በፍቅርና በሰላም ለመስራት እንዳዘጋጀት ተናግራለች።

በምርቃት ስነስርዓት የተገኙት የትግራይ  ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂ ተማሪዎች ሀገራቸውን ከድህነት ለማውጣት በተማሩት የሙያ መስክ  የድርሻቸውን እንዲወጡ መክረዋል።

“ተመራቂ ተማሪዎች  ሰላምና አንድነታችሁ አጠናክራችሁ በትግዕስት ለዚህ በመብቃታቸሁ እንኳን ደስ አላችሁ “ብለዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው”  ተማሪዎች እርስ በርሳችሁ ተደጋግፋችሁ አንድነታህቹ ጠብቃችሁ በመቻቻል ሀገራችንን ለማሳደግ  ከፍተኛ ሀላፊነት ይጠብቅባችኋል” ብለዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ  በልዩ ልዩ ሙያ ከ7ሺህ 400 በላይ ተማሪዎች አሰልጥኖ ዛሬ በመጀመሪያ ፣ ሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ ማስመረቁን የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት ገልጸዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል  26 በመቶ ሴቶች ናቸው።

ዩኒቨርሰቲው የሳሆና ኩናምኛ ቋንቋዎች ጨምሮ  በ345 የትምህርት ፕሮግራሞች ከ31ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።