የህብረተሰቡ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረግ እንደሚገባ በሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች አመለከቱ

103
ሃዋሳ ኢዜአ ሐምሌ 13/2011 ህብረተሰቡ ያለውን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር  ምላሽ  እንዲያገኝና  ሰላም ለማምጣት በጋራ መስራት እንደሚገባ በሀዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች አመለከቱ። በሃዋሳ ከተማ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በመረጋጋቱ ወደ ዘውትር  እንቅስቃሴ እየተገባ ነው። በከተማዋ የሪፈራል አካባቢ ነዋሪ አቶ መንግስቱ ጨቆርሳ እንዳሉት የተነሳው የክልልነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ሲገባ በሁከት መፍትሄ ፍለጋ የተሄደበት መንገድ ተገቢ አይደለም። ባለፉት ሁለት ቀናት ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር ሁሉንም ያስደነገጠ እንደነበር ጠቁመው መንግስት ፣የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በጋራ መስራት በመቻላቸው የከተማዋ እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞ ሁኔታ መመለሱን  ተናግረዋል። ቀድሞ የነበረውን የመተሳሰብ ፣ የመረዳዳትና ችግሮች ሲከሰቱ በጋራ ተወያይቶ የመፍታት ልምድ በመመለስ ለችግሮቻችን መፍትሄ መስጠት ተገቢ መሆኑንም  አመልክተዋል። በከተማው የቀበሌ አምስት ነዋሪ አቶ አወቀ ግርማ በበኩላቸው ላለፉት ሁለት ቀናት በሃዋሳ እንቅስቃሴው ቆሞ እንደነበረ ገልጸዋል። ዛሬ በተወሰነ ደረጃ ባጃጆችና የተወሰኑ ታክሲዎች ወደ ስራ መግባት መቻላቸው በሀረር ሰፈር አካባቢ ያሉ ንግድ ቤቶች ተከፍተው ስራ መጀመራቸው ሰውም መረጋጋት እንደቻለ ተናግረዋል። “አሁን ቀድሞ የነበረውን ሁኔታ ለመመለስ መንግስት ከሚያወራው በላይ ሰላምን ለማስከበር መስራት አለበት” ብለዋል። ለረጅም ዓመታት በሃዋሳ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጣሪ ሆነው ሲሰሩ እንደቆዩ  ተናግረው ብዙ ደስታና ችግሮችን አብሮ ያሳለፈ ህዝብ የሚለያይ ነገር ሲከሰት የሚያሳዝን መሆነ ገልጸዋል። “በህዝቦች መካከል ያለውን በጥርጣሬ የመተያየትና የሻከረ ግንኙነት ለማስተካከል   ሁላችንም በጋራ  መስራት አለብን “ብለዋል። ጎጠኝነት እና እራስ ወዳድነት ያጠፋል እንጂ ለማንም እንደማይበጅ በመገንዘብ በመነጋገር ወደ አንድነት መምጣት እንደሚገባም አመልክተዋል። በመሀል ፒያሳ አካባቢ የጀበና ቡናና ሻይ ስራ ላይ የተሰማራችው ወይዘሪት ሀረገወይን ታደሰ በበኩሏ ባለፊት ሁለት ቀናት በጭንቀትና በውጥረት ውስጥ ሆና መቆየቷን ተናግራለች። “ሰላም ሲኖርና ስራዬን መስራት ስችል ደስተኛ ያደርገኛል “ያለችው ሀረገወይን ትናንት የተከሰተውን ችግር በመርሳተ በአንድነት ለሰላም መስራት የምትደግፍ መሆኗን ተናግራለች። የጸጥታ አካላትችግሩን ለመፍታት ያካነወኑት ስራ የሚያስመሰግን መሆኑንና ሁሉም ከነሱ ጎን በመቆም የከተማዋን ሰላም ወደ ቀድሞ ሁኔታ ለመመለስ መስራት እንደሚገባም ጠቁማለች።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም