ነዋሪዎች በአረንጓዴ አሻራ ቀን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለመሳተፍ ዝግጁነታቸውን እየገለጹ ነው

79
ሐምሌ 13/2011 የአረንጓዴ አሻራ ቀን መርሃ ግብር ሊከናወን ዘጠኝ ቀናት ቀርተውታል፤ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም በሚሰሩባቸው ተቋማትና በየአካባቢዎቻቸው ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። በተያዘው ክረምት በመላ አገሪቱ 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በመንግሥት በይፋ በተጀመረው መርሐ ግብር እስካሁን በርካታ ችግኞች እየተተከሉ ነው። ይህንኑ አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም በአረንጓዴ አሻራ ቀን በሚከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በየሚሰሩበት ተቋምና በየአካባቢያቸው ለመሳተፍ ተዘጋጅተዋል። በመንግስት ልዩ ትኩረት የተሰጠው የችግኝ ተከላ የዜጎችን የመኖር ዋስታና የሚጨምር ተግባር ከመሆኑ ባሻገር እየጨመረ የመጣውን የዓለም የሙቀት መጠን ለመቀነስ ትልቅ አሰተዋጽኦ እንደሚያበረክት እምነታቸው መሆኑንም ተናግረዋል። በደን የተሸፈነች ኢትዮጵያን ዳግም ለመፍጠር መንግስት በሚያደርገው ጥረት የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩና በመኖሪያና በስራ ቦታዎች የሚተክሏቸውን ችግኞች በዘላቂነት ለመንከባከብም ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል። አስተያያት ሰጪዎቹ ችግኝ በመትከል አካባቢን ጽዱና ለጤና ተስማሚ ማድረግ ብሎም ተፈጥሮን መጠበቅ ስለሚቻል ሁሉም ለዚህ ዓላማ መቆም ይኖርበታል ብለዋል። የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ለማሳካት 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች የተቆፈሩ ሲሆን 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞችም ተዘጋጅተዋል። መርሃ ግብሩ በይፋ ከተጀመረበት ካለፈው ወር ጀምሮም በመላ አገሪቱ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ ተተክሏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም