ህብረተሰቡ ችግኝ የመትከል ባህሉን በማዳበር ጽዱና አረንጓዴ አካባቢን መፍጠር ይኖርበታል ተባለ

227

ሐምሌ 13 /2011 ህብረተሰቡ በየአካባቢ ችግኝ የመትከል ባህሉን በማዳበር አገሪቱ ምቹ፣ ጽዱና አረንጓዴ እንድትሆን አስተዋጽኦውን ማጎልበት እንደሚገባው የተለያዩ ተቋማት ሰራተኞች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ እና 30 የቢሮው ተጠሪ ተቋማት በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ የሚገኘውን የአረንጓዴ ልማት መርሃ-ግብር ዘመቻ በመደገፍ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።

የችግኝ ተከላው በአቃቂ ወረዳ ልዩ ስሙ ገንዳ ኢንሲሌ ፊንጫ በሚባል አካባቢ የተካሄደ ሲሆን ሶስት ሺህ የሚጠጉ ሰራተኞች ተሳትፈውበታል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፤ ህዝቡ ችግኝ የመትከል ባህሉን በማዳበር አገሪቱ ምቹ፣ ጽዱና አረንጓዴ እንድትሆን አስተዋጽኦውን ማጎልበት አለበት።

ተሳታፊዎቹ ችግኝን ክረምት ሲመጣ በዘመቻ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የመትከል ልምድም ሊኖር ይገባል ብለዋል  ።

በተለይም ከመትከል ባሻገር እስኪጸድቅ ተከታትሎ የማልማት ሃላፊነትን መወጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ የአንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት እና የሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት ድርጅት ሰራተኞች በችግኝ ተከላው ከተሳተፉት መካከል ሲሆኑ 10 ሺህ ችግኞችን ተክለዋል።