ተመራቂዎች ያስተማራቸውን ህዝብና ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል አለባቸው---ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም

57
ሐምሌ 13/2011 ተመራቂ ተማሪዎች ያስተማራቸውን ህዝብና ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም አሳሰቡ ። የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ በቅድመና ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ያስተማራቸው 1ሺህ 495 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል። በምርቃው ስነስዓት ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት ሚኒስትሯ  እንዳሉት መንግስት ለትምህርት ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶና ሰፊ ሀብት መድቦ እየሰራ ይገኛል ። በዚያው ልክ ተመራቂ ተማሪዎችም ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በቅንነት በማገልገል ኃላፊነታቸውን በቅንነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል ። የትምህርት ዘርፍ ተግዳሮት ሆኖ የቆየው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ በርካታ የማሻሻያ ተግባራትን እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል ። የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል በበኩላችው " ዩኒቨርሲቲው ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል "ብለዋል። እንደ ዶክተር ፋሪስ በ1999 ዓ.ም በሦስት የትምህርት ክፍል የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በስድስት  የድህረ ምረቃና በ42 የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች በማስተማር ላይ ይገኛል። ተመራቂዎቹ በንድፈ ሀሳብና በተግባር የቀሰሙትን ዕውቀት በስራ ዓለም ሊተገብሩት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። ከፋርማሲ ትምህርት ክፍል የተመረቀው አለማየሁ ትንሽኩ በሰጠው አስተያየት በትምህርት ቆይታው በቂ ዕውቀት ማግኘቱን ገልጾ ”ወደስራ ስገባ በሙሉ አቅሜ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ” ብሏል። ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው  ተማሪዎች መካከል 534 ሴቶች ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም