የወለጋና የአሶሳ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ችግኝ ተከሉ

167

ሐምሌ 13 / 2011 ዓ.ም. አሶሳ ኢዜአ፡ የወለጋና የአሶሳ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ክለቦች ሀገር አቀፉን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለማሳካት በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ችግኝ ተከሉ ።

የሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች አመራሮች በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በሃገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮው ክረምት አራት ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ለማካሄድ የተያዘው እቅድ እንዲሳካ የድርሻቸውን ለመወጣት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ዶክተር ከበደ ነሞምሳ  ዩኒቨርሲቲው የመደበኛና የክረምት ተማሪዎችንና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በማስተባበር ችግኞች በስፋት እየተከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተጎራባች ክልሎችን ምሁራንና ህዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር አንዳቸው ወደ ሌላቸኛው አካካባቢ በመሄድ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ማከናወንና የወዳጅነት ስፖርታዊ  ውድድሮች ማካሔድ መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ናሆም ጀምስ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው በዚህ ክረምት በሺዎች የሚቆጠሩ ችግኞች ተዘጋጅተው እየተተከሉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

“እየተተከሉ ከሚገኙ ችግኞች መካከል አብዛኞቹ ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸው ማንጎ ብርቱካን፣ አቮካዶና ቀርከሃ ያካተቱ ናቸው “ብለዋል፡፡

የመተከሉት ችግኞች በዘላቂነት እንዲጸድቁ  የሰው ኃይል መድቦለት እንክብካቤ እያደረገ እንደሚገኝም አቶ ናሆም ገልፀዋል ።

በችግኝ ተከላው ከተሳተፉት መካከል በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ነጻ የትምህርት እድል የተሰጠው ደቡብ ሱዳናዊው ኢማኑኤል ኬኚ በሰጠው አስተያየት ኢትዮጵያዊያን የሚያካሂዱት የችግኝ ተከላ ስራ ከሃገሪቱ አልፎ ምስራቅ አፍሪካን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጿል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሶሳ ከተማ የሚገኙ የኤም.ኤ. እና የሮሜድ ሜዲካል ኮሌጆች ያስመረቁዋቸው ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች የችግኝ ተከላ ስራ አካሄደዋል፡፡