የጓዳ ምሬትና ለቅሶ

ጎረቤቴ የሶሰት ልጆች እናት ናቸው። በየእለቱ ጠዋት ወደ ስራ ስሄድና ማታ ስመለስ በሀዘን በተሰበረ ድምጸት ስለኑሮ ውድነት ይነግሩኛል። ስሜታቸውን የሚያጋሩኝ እኔና ቤተሰቤ በኑሮ ውድነት ያልተቸገርን ስለሚመስላቸው አይደለም። ይልቁኑ የሶስት ልጆች እናት ብሶታቸውን የሚነግሩኝ በመገናኛ ብዙሃን ውስጥ መስራቴን ስለሚያውቁና አንዳች ተአምር በመፍጠር የኑሮ ውድነቱ ፈር እንዲይዝ እንድንሰራ ለማድረግ አስበው መሆኑን እገነዘባለሁ። በአሁኑ ወቅት ለሸቀጦች ዋጋ መናር፣ ለትራንስፖርት ዋጋ በሁለትና ሦስት እጥፍ መጨመር፣ ለነዋሪው ኪስ መራቆት፣ ለችግርና ጉስቁልና  መጋለጥ፣ ወዘተ… ሰበቡ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ስለመሆኑ ከነጋዴዎች አንደበት ብንሰማም እውነታው ግን የተለየ ነው። ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር በአገልግሎትና በሸቀጦች ላይ ዋጋ በመጨመር የራሳቸውን ሀብት ለማካበት ሌት ተቀን የሚሰሩ ያልጠግብ ባይ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ተግባር መሆኑ ግልጽ ነው። ለአብነት የዛሬ አስራ አንድ ዓመት የኢትዮጵያ ሚሊኒዬም በዓል ሲከበር የታየው የኑሮ ውድነት በተመሳሳይ መልኩ ሊታወስ ይችላል። በወቅቱ በሸቀጦችና አገልግሎቶች ላይ የተከሰተው የዋጋ ንረት የአገሪቷ "እድገት ያመጣው ነው" የሚል ትንታኔ ቢሰጠውም እስካሁን በተረጋጋ መልኩ ከመቀጠል ይልቅ እየናረ መሄዱን ማንም ሊገታው አልቻለም። የኑሮ ውድነት በዚህ ዓመት እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ብዙዎችን እያማረረ ነው። ሌላውን ዝርዝር ነገር ትተን አሁን ያለው የምግብ እህል ዋጋ ስንመለከት ከአንድ ወር በፊት ከነበረው የዋጋ ምጣኔ ጋር ልዩነት እያሳየ ነው። ለአብነት ከወራት በፊት ሁለት ሺህ ብር ይሸጥ የነበረው 100 ኪሎ ግራም ሰርገኛ ጤፍ አሁን ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ብር፣ አንድ ኪሎ ግራም ምስር ከ60 ብር ወደ 80 ብር፣ ቀይ ሽንኩርት ከ12 ብር ወደ 27 ብር አሻቅቧል ።የዳቦ እርሾ ከ400ብር ወደ ሁለት ሺ ብር አሻቅቧል። ዘይት፣ ፓስታ፣ ዳቦ፣ ሩዝ ሁሉም በዋጋ ንረት ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል። ጉረቤቴንም ያማረራቸው ይህ ያለምክንያት እያደገ የመጣው የዋጋ ጭማሪ ነው። በመንግስት በኩል ለህብረተሰቡ ይቀርብ የነበረው የአትክልት ዘይት ለምግብነት መዋሉ አደጋው ከፍ ያለነው መባሉን ተከትሎ የኑግ እና የሱፍ ዘይት ጭማሪ ማሳየታቸው የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል። ለዚህ የዋጋ ንረት መባባስ ምክንያቱ በህግና በሞራል ከሚመራው የንግዱ ማህበረሰብ መካከል የራሳቸውን ፍላጎት ለማርካት ብቻ የሚተጉ ስግብግብ ነጋዴዎች መኖራቸው ነው። በርግጥ በቁጥራቸው ጥቂት የማይባለው ነጋዴዎች ጎረቤቴና መሰል እናቶችን ማስለቀሱ ፍጹም አይሰማውም፡፡ በተረጋጋና የህዝብን የኑሮ ደረጃ በማይጎዳ መልኩ ነግዶ በማትረፍ የሚያምኑ ጥቂቶች መሆናቸው አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። የህዝብ ኑሮ ሲረጋጋ፣ ሰላሙ ሲጠበቅ፣ በኑሮ እየተጎዳ አቅሙ ሳይዳከም የንግድ ልውውጥ በማድረግ ውጤታማ መሆንን የሚያምኑ ጥቂቶች መሆናቸው ለችግሩ መባባስ መንሰኤ ነው። በህገወጥ መንገድ የማይገባቸውን ትርፍ ለማግበስበስ የሚጥሩ ነጋዴዎች ከጥቅማቸው በሻገር የሚያስቡት፣ አርቀው የሚያዩት እውነት የለም። አርቀው ቢመለከቱ የሕዝብና የአገር ሰላም ከሌለ ነግዶ ማትረፍ፤ በሀብት ላይ ሀብት መከመር ይቅርና የያዘውንም መብላት እንደማይችልና እንደሚያጣ፣ ንግዱም እንደሚቆም የተረዱና የተገነዘቡ አይደለም፡፡ ጥቂት ነጋዴዎቻችን እኔንና መሰል ምስኪኖችን የሚጎዱ፣ የሚያስለቅሱ፣ የሕዝብ ችግር ለእነሱ የተለየ ደስታና ፈንጠዝያ የሚሆንላቸው፣ በስቃዩና በችግሩ የሚፈነድቁ መሆናቸው ሳያንስ የህግና የሞራል ተጠያቂነታቸውን ዘንግተውታል። በአሁኑ ወቅት ያሉ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች የሆነ አጋጣሚን ተጠቅመው የዘረፋ ሰይፋቸውን የሚመዙ፣ በግፍ ሕዝብን የሚመዘብሩ፣ የሚገፉና የሚያስለቅሱ ናቸው። ከሕግና ከዋጋ ተመን በላይ የሚሸጡ፣ የሸቀጦችን እጥረት ሆን ብሎ ለመክበር ሲሉ የሚፈጥሩ፣ ምርት በመደበቅና "የለም" በማለት እንዲሁም በስውር ዋጋ ጨምሮ በመሸጥ የሚከብሩ፣ ስኳር ቤትና መጋዘናቸው ደብቀው ሕዝብ ሲንጫጫ ለመክበር ግዜው አሁን ነው ብለው የሚነሱ ፤ በሕጻናት እምባና ለቅሶ ለማትረፍ የሚተጉ ናቸው። የሞራል ሰብዕና የላቸውም። በህግ ተጠያቂ መሆናቸውን ዘንግተውታል። አምላካቸውንም አይፈሩም። ዛሬ የሆነ ነገር ቢሰማ የእቃዎች እና የሸቀጦች እጥረት ያጋጥማል፤ "አለ" የሚሉት በሚያስደንቅ ፍጥነት ዋጋውን ያንሩታል። አንዴ ከጨመረ መቀነስ የሚባል ነገር አይኖርም። የሚጠይቃቸውም የለም።  በዓለማችን ላይ የሸቀጦችም ሆነ የእቃዎች ዋጋ አንዴ ከጨመረ ተመልሶ የማይወርድባት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አትቀርም፡፡ የአገራችን አብዛኛው ነጋዴዎች የዘ ልማድ ነጋዴዎች ናቸው። የአንድ ምርት እጥረት ሲያጋጥምና ዋጋ ሊጨምር እንደሚችልና ያ ምርት ደግሞ ሲትረፈረፍ ተመልሶ ዋጋው ወደ ነበረበት እንደሚመለስ አያውቅም፤ ቢያውቅም ስለመቀነስ ማሰብ አይፈልግም፡፡ ይሄ ደግሞ የገበያ ህግጋትን ከመጣሱም በላይ ሕዝቡን በእጅጉ ይጎዳል፡፡ የዋጋ ንረት መንስዔዎች በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙንኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ  እንደገለጹት አንዳንዴ የዋጋ ንረት ከውጭ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የመጨመሩ ምክንያት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አሁን የህብረተሰቡን ኑሮ እያናጋ ያለው በአገር ውስጥ የሚመረቱ የግብርና ምርቶች ላይ የተከሰተው ጭማሪ ነው። እነዚህን ምርቶች ለማምረት በአብዛኛው በውጭ ምንዛሬ የሚገዛ ግብዓት የማይጠይቁ መሆናቸው ይታወቃል። በከፍተኛ ደረጃ በአገር ውስጥ ግብአትን የሚጠቀሙና የሰው ጉልበትን መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው አሁን በተከሰተው ደረጃ የዋጋ ንረት ሊያጋጥም የሚችልበት ሁኔታ እንደማይስተዋል ነው ያመለከቱት። አቶ ወንድሙ «የመጀመሪያው መንስኤ የግብይት ስርዓት ችግር ነው። የግብይት ስርዓቱ በጣም የተንዛዛ ሲሆን፤ ደላሎች በአምራችና ምርቱን ገበያ ላይ በሚያቀረበው ነጋዴ መካከል በመሆን ከነጋዴው ጋር በመመሳጠር ዋጋ ይወስናሉ። በገበሬው ምርት ላይ ፈላጭ ቆራጭ ይሆናሉ። ምርቱ ገበያ ላይ ሳይገባ ደላላው በስልክ ብቻ በመጠቀም ምርቱ ከተመረተበት ቦታ ሳይነሳ የዋጋ ድርድር በማድረግ ዋጋ ይዋዋላሉ። «ከዚህ ባለፈ በህገ ወጥ ደላሎች ተዋናይነት ምርት የማዞር፣ የማሸሽ፣ የማቆየት እንዲሁም ቀን ጠብቆ ዋጋ በመጨመር በህገ ወጥ መንገድ ሀብት ለማካበት የሚደረግ ሴራ ሲሆን፤ አሁን ላይ የተስተዋለው የዋጋ ጭማሬ በምርት እጥረትና በአሳማኝ ምክንያት የተከሰተ ሳይሆን በደላሎች የተቀነባበረ በሰው ሰራሽ መንገድ የተፈጠረ የዋጋ ንረት ነው። ዳይሬክተሩ የግብይት ስርዓቱ ህገ ወጥነት የሚሰፍንበትና በየጊዜው ዋጋው እየናረ የሚሄድበትን ምክንያት ሲገልፁ፤ «ህብረተሰቡ ግብይቱን በደረሰኝ ስለማይፈፅምና ግብይቱ በእውቀት ሳይደገፍ በተለምዶ የሚከወን በመሆኑ ለህገ ወጥ ደላሎች ተጋላጭ በመሆን ሁሌም የዋጋ ንረት እንዲኖር ምክንያት ሆኗል» በማለት ነው የገለጹት። መፍትሄ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደታየው ከነፃ ገበያ የውድድር መርህ ውጭ በሆነ አካሄድ ላይ ተሰማርተው የተገኙ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ ነጋዴዎቹ እርምጃው የተወሰደባቸው ሸቀጦችን ሆን ብሎ በመጋዘን በማከማቸት ወይም በመደበቅ፣ በሸቀጦች ላይ ያለአንዳች ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግና በመሳሰሉ ተግባራት ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው መሆኑ መገለጹም አይዘነጋም፡፡ ከአስተዳደራዊ እርምጃው በተጨማሪ አጥፊዎቹን ለሕግ ለማቅረብ የሚመለከተው አካል በጥንካሬ ሊገፋበት ይገባል፡፡ ይህ ሒደት የሚቀጥል ከሆነ ነጋዴዎቹ ክፋታቸውን ማረቅ የሚችሉበት እድል ይሰጣቸዋል። በየትኛውም የአገሪቷ ክፍል የሚገኙ ነጋዴዎች እንደወትሮው ሁሉ ሕግና ደንብን አክብረው በውድድር ላይ የተመሰረተ የንግድ ሥራቸውን ማካሄድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ደንብን በመተላለፍ ያልተገባ ጥቅም ለማጋበስ የሚደረግ ሙከራ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ለተጠያቂነት የሚዳርግ ወንጀል መሆኑን በውል ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ቀደም ብለው የገቡ ሸቀጦችን "ወደፊት በተጋነነ ዋጋ እሸጣለሁ" በሚል እሳቤ በመጋዘን ማከማቸት ወይም መደበቅ "አሁንም በፈለኩት ዋጋ መሸጥ እችላለሁ" በሚል ድፍረት ሕዝብን ለመበዝበዝ መሞከር ወንጀል ነው፡፡ የነፃ ገበያ መርህን በመጣስ ዋጋን በስምምነት የመወሰን ተግባር ሁሉ የገበያ አለመረጋጋትን ስለሚያስከትል በቸልታ የማይታለፍ መሆኑ አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል፡፡ መንግስት ለሕዝቦቹ ጥቅም መጠበቅ በትጋት እንደሚሰራ በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጣል ። ቃሉን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ በሕዝብ ላይ የሚደርስን ማንኛውንም ጉዳት ለማስተካከል የሚረዱ እርምጃዎቹን በማጠናከር ህገ ወጦች እጃቸውን ከጥፋት እንዲሰበስቡ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ያን ጊዜ እንደጎረቤቴ ያሉ እናትና መሰሎቻቸው፣ እኔና ቢጤዎቼ፣ በቀን ሶስቴ ለመብላት የከበዳቸው ወገኖቼ፣ በየጥጋጥጉ ቆመው የሚቆዝሙ ነፍሶች እፎይታ ያገኛሉ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም