ሰሜን ሸዋን ወክለው በፓራ ኦሎምፒክ የተሳተፉ 25 ስፖርተኞች ተሸለሙ

60
ደብረ ብርሃን ሰኔ 4/2010 በመላው አማራ ስፖርታዊ ውድድር ሰሜን ሸዋን ወክለው በፓራ ኦሎምፒክ የተሳተፉ 25 ስፖርተኞች ከዞኑ ስፖርት መምሪያ የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተላቸው፡፡ በባህርዳር ከተማ ከመጋቢት 15 እስከ 29 ቀን 21010 ዓ.ም በተካሄደው ስድስተኛው የመላው አማራ ስፖርት ውድድር በአጭር ርቀት ሩጫ፣ በአሎሎና ዲስክ ውርወራ ተሳትፈዋል። በዚሁ የፓራ ኦሎምፒክ ስፖርት የተሳተፉ ስፖርተኞች 19 የወርቅ፣ 9 ብር እና 6 ነሃስ ሜዳሊያ አምጥተው ውድድሩን በአንደኝነት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡ በውድድሩ ተሳትፈው ውጤት ላስመዘገቡት ስፖርተኞች ትናንት ማምሻውን በደብረ ብርሃን ከተማ የእራት ግብዣ የተደረገላቸው ሲሆን ለእያንዳንዳቸውም ሙሉ ትጥቅና የማበረታቻ የገንዘብ ድጋፍ ተበርክቶላቸዋል፡፡ ስፖርተኞቹ በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ቀጣይ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የዞኑ ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክላል ሳህለማሪያም በሽልማቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡ ''በዞኑ የአትሌቲክስ ስፖርትን ለማሳደግ በተደረገው ጥረትና ድጋፍ በተለይ በፓራ ኦሎምፒክ  ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ ነው'' ብለዋል፡፡ አትሌት መርሻ መብራቴ በበኩሏ መምሪያው ያበረከተላቸው የማበረታቻ ሽልማት ጠንክረው በመስራት የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ተናግራለች፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም