ነዋሪዎቹ ክረምቱን ተከትሎ በሚከሰት የጎርፍ አደጋ ስጋት ላይ ወድቀናል አሉ

71

ሐምሌ 13 /2011 ክረምቱን ተከትሎ በሚከሰት የጎርፍ አደጋ ስጋት ላይ መውደቃቸውን ችግሩ ያሳሰባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የሚመለከታቸው ተቋማት ደግሞ ሊከሰት ሚችለውን ችግር ለመከላከል እየሰራን ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች  እንደተናገሩት የጎርፍ አደጋ ስጋቱ  በዕለት ተዕለት የስራ እንቅስቃሴያቸው ላይ ጫና መፍጠሩን፤ ለህይወታቸውና ለንብረታቸው ምንም ዋስትና እንደሌላቸው ተናግረዋል።

በአከባቢያቸው በክረምት ዝናብ  ምክንያት በሚከሰት የጎርፍ አደጋ አረጋውያን ና ህፃናትን ቤት ጥሎ ስራ ለመሄድ መቸገራቸውንና ስጋት ላይ መሆናቸውን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰውነት ይልማ ይገልጻሉ።

በየቦታው በሚጣሉ የውሃ መያዣ ላስቲኮች፣ ፌስታሎች እና በሌሎች ተረፈ ምርቶች ምክንያት የውሃ መፋሰሻ ቱቦዎች መዘጋት የችግሩ ዋና መንስዔ መሆኑንም የተናገሩት አቶ ሰውነት፤ ጎርፉ በአስፓልት ላይ በመፍሰስ  ወደ መኖሪያና ንግድ ቤቶች እየገባ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል።

የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ እሸቱ ከበደ  በበኩላቸው  የጎርፍ አደጋ ችግር ከግዜ ወደ ግዜ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ስጋት እንዳሳደረባቸው ገልጸው፤ ችግሩ እንዲባበስ ያደረገው በቅርቡ የተገነባ መንድ የጥራት መጓደል እንደ ሆነ ነው የሚናገሩት።

በቅርቡ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በአካባቢው የተገነባው የአስፓልት መንገድ ከጣፎ አያት ቁጥር-2 የጋራ መኖሪያ ቤቶች አቅራቢያ ሲደርስ የውሃ ማፋሰሻ ባለመሰራቱ ከየአቅጣጫው የሚመጣ ጎርፍ ወደ መኖሪያ ቤቶች እየገባ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የችግሩን አሳሳቢነት ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም እስካሁን   ምላሽ አለማግኘታቸውን ነው አቶ እሸቱ  የጠቆሙት።

በከተማዋ የሚስተዋሉ የጎርፍ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰተ በኋላም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ደግሞ  የሚመለከታቸው ተቋማት የሚገልጹት።

የደረቅ ቆሻሻ ክምችት ወደ ውሃ ማፋሰሻ ቱቦዎች እንዳይገባና በጎርፍ አደጋ  በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ  በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ሳሙዔል ገንዘብ አስታውቀዋል።

ቆሻሻን የማስወገድ ስራ የኤጀንሲው የዘወትር ተግባር ቢሆንም ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ሊከሰት የሚችለውን ጉዳት በመረዳት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ   እየተሰራ  መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ኤጄንሲው ዋና ዋና መንገዶችን የሚያፀዱ በየክፍለ ከተማው በአማካይ ከ 4 ሺህ 600 በላይ ሰራተኞችን፤ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን የሚያፀዱ ደግሞ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች በሴፍቲኔት ማሰማራቱን ባለሙያው ገልጸዋል።

ከሰው ሃይል በተጨማሪም የደረቅ ቆሻሻ ማንሻ ማሽኖችን እያሰማሩ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሳሙኤል፤ የከተማዋ የመንገድ ግንባታ ደረጃ ውስንነት ለስራው እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዋል።

በመንገድ ዳር ያሉት የፍሳሽ ማስተላለፊያዎች(ዲቾች) አብዛኛዎቹ ክዳን የሌላቸው፤ ክዳን ያላቸውም ተገቢውን አገልግሎት ሳይሰጡ የሚሰባበሩ በመሆኑ በተለያዩ ደረቅ ቆሻሻዎች በመዘጋታቸው  የፅዳት ሥራውን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ነው ያነሱት።

በክረምት ወቅት ለሚከሰት ጎርፍ  ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም የመንገድ ጥራት ጉድለት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ የገለፁት ደግሞ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጡኡማይ ወልደገብርዔል ናቸው።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በመንገድ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችና  ከህብረተሰቡ የሚነሱ  ቅሬታዎችን  በዘላቂነት ለመፍታት  ባለሥልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ  እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን በበኩሉ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል የተለያዩ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጠ መሆኑን ገልጿል።

በዚህ ክረምት ከአለፉት አመታት ልምድ በመውሰድ በከተማዋ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ 100 ቦታዎች ተለይቶ፤ ቤት ለቤት በመዘዋወር ለነዋሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ስለሽ ተስፋዬ ገልፀዋል።

ባለስልጣኑ አደጋ ሲከሰትም በፍጥነት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ 26 ተሽከርካሪዎችን ገዝቶ ወደ ስራ አሰማርቷል።

ከተሰማሩት ተሽከርካሪዎች መካከል 10ሩ በጎርፍ ምክንያት ለሚከሰቱ አደጋዎች ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በ2011 ዓ.ም በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ከ3 ሚሊዮብ ብር በላይ የሚገመት ንብረት ማትረፍ መቻሉንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም