ዓዋጁ የተበታተነውን የሰው ኃይል በማደራጀትና በማቀናጀት ለአገሩ ልማትና እድገት ያስችለዋል- የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ወጣቶች

67
ነቀምቴ ሐምሌ 13 / 2011 የዜግነት አገልግሎት ዓዋጅ የተበታተነውን የሰው ኃይል በማደራጀትና በማቀናጀት ለክልሉ ብሎም ለአገሩ ልማትና እድገት እንደሚያስችል የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ወጣቶች ገለጹ። በሻምቡ ከተማ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ባወጣው ዓዋጅ ላይ ውይይት ተካሂዷል። ተሳታፊዎቹ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ዓዋጁ የሰው ኃይል ውጤታማ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል ያበቃል የሚል እምነት አሳድሮባቸዋል። ከተሳታፊዎቹ መካከል የሆሮ ወረዳ ነዋሪ ወጣት መሐመድ ሐሰን ዓዋጁ  ዜጎች አንድነታቸውን ባጠናከረ መልኩ ለመንቀሳቀስ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። የሻምቡ ነዋሪ ወይዘሮ የሺ ዋቅጅራ በበኩላቸው ዓዋጁ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል። ኅብረተሰቡ አንድነቱን በማጠናከርና የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ለአገሩ ዕድገት ለመሥራት እንደሚያስችለው ገልጸዋል። ሌላው ወጣት ተመስገን ጋቡሽ  ዓዋጁ ዜጎች የጋራ አገር ባለቤት መሆኑን ከማረጋገጡም በላይ፤ወጣቱን ትውልድ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንደሚያደርግ አስታውቋል። እንደ አገር ለማደግና ወደፊት ለመራመድ የዜጎች ተሳትፎና ቅንጅት አቅጣጫ ጠቋሚ መሆኑን ያወሳው አስተያየት ሰጪው፣ በተፈጥሮ ሃብት፣የበአካባቢ ጥበቃና በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ አንድነትን መሥራት ይገባናል ብሏል። የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጃባ አዱኛ ዓዋጁ  ዜጎች በዕድሜ፣በፆታ፣በትምህርት ደረጃ ሳይለያዩ በፍላጎት ላይ በተመሰረቱ ተግባራት ለመሳተፍ እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል። ዜጎች ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለባቸውና የሰላም ዋስትናቸውን በራሳቸው ማረጋገጥ እንዳለባቸውም አመልክተዋል። የኦሮሚያ  ክልል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤባ ገርባ ዓዋጁ ዜጋው መብትና ግዴታውን ለይቶ በመረዳት በአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ድርሻውን ለመወጣት እንደሚያበቃው አስረድተዋል። በውይይቱ ከከተማዋና ከዘጠኝ የገጠር ወረዳዎች የተውጣጡ ከ560 በላይ ወጣቶች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም