በትግራይ ለስፖርት ዘርፍ ድጋፍ ላደረጉ 80 ባለሃብቶችና ባለሙያዎች እውቅና ተሰጠ

56
መቐለ ኢዜአ ሓምሌ 13/2011 ዓ.ም የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የክልሉን ስፖርት በማበረታታት አርአያ ለሆኑ 80 ባለሃብቶችና የስፖርት ባለሙያዎች የእውቅና ምስክር ወረቀት ሰጠ። ቢሮው የእውቅና ምስክር ወረቀት ትናንት የሰጠው ለ60 ባለሃብቶችና ለ20 የዘርፉ ባለሙያዎች ነው። በእውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ ወቅት የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ገነት አረፋ እንዳሉት በክልሉ መንግስት እውቅና የተሰጣቸው ባለሃብቶች እያንዳንዳቸው ከ25 እስከ 45 የሚሆኑ ታዳጊ ስፖርተኞችን በማቀፍ በየወሩ ለቀለብና ለስፖርት ትጥቅ ገንዘብ በመመደብ የክልሉን የስፖርት ዘርፍ ለማነቃቃት እገዛ ያደረጉ ናቸው ። በስፖርት ዘርፍ ሙያው የተሰማሩ 20 ባለሙያዎች ደግሞ ታዳጊ ወጣት ስፖርተኞቹን ያለ ምንም ክፍያ በሳምንት ሶስት ጊዜ ነጻ የስልጠና አገልግሎት በመስጠት ለውጤት ያበቁ መሆናቸውን  ገልጸዋል። በተቀናጀ ድጋፍ ክልሉንና ኢትዮጰያን ወክለው በብስክሌት፣ ቴንስ ፣ ቼዝ፣ እግር ኳስና ቦሊቦል እንዲሁም ቴኳንዶና ማርሻል አርት የሚወዳደሩ ብቁ ስፖርተኞች እንዲወጡ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል። "ስፖርት ከመንግስት እጅ ወጥቶ ወደ ግል ባላሃብቶች ለማዘዋወር እየተሰራ ነው" ያሉት ወይዘሮ ገነት "አቅም ያለው የህብረተሰብ ክፍል የክልሉን የስፖርት ዘርፍ ለማበረታታት ሊያግዝ ይገባል "ብለዋል። እውቅና ከተሰጣቸው ባለሙያዎች መካከል በምስራቃዊ ዞን በፍረወይኒ ከተማ የአትሌቲክስ ስፖርት አሰልጣኝ አቶ ጌታቸው ተክላይ በሰጡት አስተያየት" መንግስት ለስፖርት ዘርፉ እድገት ልዩ ትኩረት ከሰጠው እኛም የማያቋርጥ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ነን "ብለዋል። ባላቸው  አቅም ማገዝ ለግለሰቦች ጥቅም ብቻ ሳይሆን የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን  መልካም ስም ለማስጠራት  ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ደግሞ በምዕራባዊ ዞን ሁመራ ከተማ ስፖርተኞችን በመደገፍ እውቅና የተሰጣቸው ባለሃብት አቶ ስዩም ገብረ ማሪያም ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም