በአማራ ክልል አንድ ቢሊዮን 700 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል እየተሰራ ነው

62
ባህር ዳር ኢዜአ ሀምሌ 13/2011 በአማራ ክልል ከየአካባቢው ስነ-ምህዳር ጋር ተስማሚ የሆነ አንድ ቢሊዮን 700 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ። በክልሉ የተዘጋጀውን ችግኝ ለመትከል እየተካሄደ ያለው ስራ  “40 ችግኝ ለአንድ ሰው ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው። በቢሮው የደን ልማት ባለሙያ አቶ እስመላለም ምህረት ለኢዜአ እንዳሉት የችግኝ ተከላው በበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በተከናወነባቸው ፣ ለደን በተከለሉ፣ በወል፣ በተራቆቱና በሞዴልነት በተመረጡ  ቦታዎች  የሚካሄድ  ነው። የክልሉ ህብረተሰብ ቀደም ብሎ ጉድጓዶችን በማዘጋጀት ካለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ በየአካባቢው ችግኞቹን  የመትከል ስራ ላይ ይገኛል። በተለይ በምዕራብ አማራ አካባቢ ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ ዝናቡ በአጥጋቢ ሁኔታ መጣል በመጀመሩ እስከ አሁን ድረስ ከ351 ሚሊዮን በላይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በ68 ሺህ 452 ሄክታር መሬት ላይ እንዲተከል ተደርጓል። "የዘንድሮውን የችግኝ ተከላ ከወትሮው ለየት የሚያደርገው ከየአካባቢው ስነ ምህዳርና የአየር ፀባይ ጋር ተስማሚ የሆኑ ችግኞችን ለይቶ እንዲዘጋጁ በማድረግ ተከላው መጀመሩ ነው " ሲሉ ባለሙያው አመልክተዋል። ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ፕሮግራምም በክልሉ 100 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ቀን ለመትከል ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል። ህብረተሰቡም የሚተክላቸውን ችግኞች በባለቤትነት ስሜት ጠብቆና ተንከባክቦ በማሳደግ በክልሉ አሁን 64 በመቶ ያለውን አማካኝ የመጽደቅ ምጣኔ ወደ 75 በመቶ ለማሳደግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ተብሏል። በዘንድሮው የክረምት ወቅት እየተተከለ ያለው ችግኝ የክልሉን አጠቃላይ የደን ሽፋን አሁን ካለበት 14 በመቶ ወደ 15 በመቶ እንደሚያሳድገው ከባለሙያው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ። በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ የኮለል ለቻ ቀበሌ አርሶ አደር ስሜነህ ሞላልኝ በሰጡት አስተያየት የመትከያ ጉድገዶችን ቀድመው በማዘጋጀት ተከላውን በተሳካ ሁኔታ እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል ። ችግኝ የሚያስገኘውን ጥቅም ቀድመው በመረዳታቸው ምክንያት የተተከሉት ችግኞች በመኮትኮትና በማረም ተንከባክበውና ጠብቀው እያሳደጉ መሆናቸውን አስረድተዋል። በበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት የተከናወነበትን ተፋሰስ በስነ-ህይወታዊ ዘዴ አጠናክረው ማጠናቀቃቸውን የተናገሩት ደግሞ በዚሁ ወረዳ የአባይ ሳንግብ ቀበሌ አርሶ አደር ደባስ አላምረው ናቸው። በአዊ ዞን ጓጉሳ ሽኩዳድ ወረዳ የአስኩና አግዛ ቀበሌ አርሶ አደር ምህረቴ አዳም እንደገለጹት ደግሞ  ከተያዘው  ዓመት በፊት በተጎዳ 13 ሄክታር የወል መሬት ላይ ከ50ሺህ በላይ የተከሉትን የደን ችግኝ ጥበቃ በመቅጠር ተንከባክበው አሳድገዋል። በተያዘው የክረምት ወቅትም ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በመሆን  ተጨማሪ 10 ሺህ  የደን ችግኞችን ተክለው ማጠናቀቃቸውን አስረድተዋል። ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት በክልሉ ከተተከለው ከአንድ ቢሊዮን  ችግኝ በላይ ውስጥ 64 በመቶው መፅደቁን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም