ተመራቂዎችንና ቀጣሪ ተቋማትን የሚያገናኝ ዓውደ-ርዕይ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ተዘጋጀ

117

ሐምሌ  (ኢዜአ)12/ 2011 ተመራቂዎችንና ቀጣሪ ተቋማትን የሚያገናኝ የሁለት ቀናት ዓውደ-ርዕይ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ተዘጋጀ።
ዛሬና ነገ በሚቆየው የተመራቂዎችንና ቀጣሪ ተቋማት ዓውደ ርዕይ ቀጣሪዎች የሚፈልጓቸውን ተመራቂ ተማሪዎችን ለማግኘት የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

ተመራቂዎች በበኩላቸው የቀጣሪዎችን ፍላጎት ለመረዳት የሚያስችላቸው አጋጣሚ እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።

የዓውደ-ርዩ መዘጋጀት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የትምህርት መርሃ ግብራቸውን የወቅቱ ገበያ በሚፈልገው መንገድ ለመቃኘት እንደሚያስችላቸው የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዲን አቶ ራህመቶ በየነ ገልጸዋል።

ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ለ36ኛ ጊዜ የሚያስመርቃቸውን 1 ሺ 500 ዕጩ ተመራቂዎችን እና ከ70 በላይ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕና ሌሎች 26 ኩባንያዎች በተሳተፉበት በዚህ የተመራቂዎችና የቀጣሪዎች ዓውደ ርዕይ ለተመራቂዎች የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወን ተናግረዋል።

”የዓውደ-ርዕይው ዓላማ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተበራከተውን የስራ አጥነት ቁጥር መቀነስ ነው” ያሉት አቶ ራህመቶ፤ ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠውን ፕሮግራም በቀጣሪዎች ፍላጎት መሰረት ማስተካከያ ለማድረግ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

ዓውደ ርዕዩ የዩኒቨርሲቲውን ፕሮግራሞች ዘመኑ በደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃና የገበያ ሁኔታ በመፈተሽ አስቀድሞ የተመራቂ ተማሪዎችን ክፍተት የሚሞሉ ተጨማሪ ስልጠናዎችን ለመስጠት የሚያስችል መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር አቶ ራህመቶ ተናግረዋል።

ዕጩ ተመራቂዎችም በትምህርት ዝግጅታቸውና ፍላጎታቸው ከኩባንያዎቹ ጋር እንዲገናኙ፣ እንዲተዋወቁ፣ ስለኩባንያዎቹ መረጃ መለዋወጥ እንዲችሉ በማድረጉ የአውደ-ርዕይውን መካሄድ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ስራ ፈላጊዎች ቀጣሪ ተቋማትን ከጋዜጣ ሲፈልጉ እንደምታውቅ የገለፀችው በማርኬቲንግ ማኔጅመንት የትምህርት ክፍል ዕጩ ተመራቂ ተማሪ ሣራ ቀኝያለው፤ ሁሉንም በአንድ ቦታ አግኝታ ያለምንም እንግልትና ወጪ ተቋማቱ ጋር ስለቅጥር ሁኔታ መወያየት መቻሏን ጠቁማለች።

በዚህም የምትፈልጋቸውን ተቋማት በማነጋገር መረጃ ለማግኘት እንዳስቻላትና ሲቪና ሌሎች መረጃዎችን መለዋወጥ እንዳገዛት አስረድታለች።

በአውደ ርዕዩ ላይ የተሳተፉ ኩባንያዎች ተወካዮች ተመራቂዎችን በፍላጎታቸው መሰረት በመለየት ተጨማሪ ሂደትን በማካሄድ ለመቅጠር የሚያስችላቸውን አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ተመሳሳይ አውደ-ርዕዮች በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቢዘጋጅ በቀላሉ ስራና ሰራተኛን ማገናኘት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ከመዋዕለ ህጻናት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ 14 ሺህ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛል።