በኦሮሚያ ክልል የሚተገበረው የዜግነት አገልግሎት ዓዋጅ የኦሮሞ ባህልና እሴቶችን ለማስመለስ ያስችላል- የነቀምቴ ነዋሪዎች

64
ነቀምቴ ሐምሌ 12/2011 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የሚተገበረው የዜግነት አገልግሎት ዓዋጅ የኦሮሞን ባህልና እሴቶች ለማስመለስ እንደሚያስችል በነቀምቴ ከተማ በጉዳዩ ላይ የመከሩ ተሳታፊዎች ተናገሩ። ከተሳታፊዎቹ አንዳንዶቹ  በሰጡት አስተያየት ዓዋጁ መልካም ባህልና እሴቶችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚያስችል ገልጸዋል። ከከተማው ነዋሪዎች አባ ገዳ ጅረኛ ገመዳ አስተያየት የተደነገገው ዓዋጁ የተረሱ የኦሮሞን ባህልና እሴቶችን ለማበልጸግ ከማስቻሉም በላይ፤ለተግባራዊነቱ ድርሻዬን ለመወጣት ያስችለኛል ብለዋል። ዓዋጁ የይቅርታ፣የፍቅር፣የመቻቻልና የመተጋገዝ ባህል እንዲዳብርና የኦሮሞ ሕዝብ መለያ የሆነውን የገዳ ሥርዓት እሴቶች እንዳሉት የተናገሩት ደግሞ ቄስ ኦሊ ጎሹ ናቸው። በኢኮኖሚ፣በማህበራዊና በፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ዜጎች በአንድነት፣በቅንጅትና በአብሮነት እንዲቀሳቀሱ ለማድረግ ሚናው ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል። ሌላኛው ተሳታፊ ወይዘሮ ርስቴ ጨምር በበኩላቸው ዓዋጁ የሥራ ባህልን ከማዳበር በተጨማሪ አንድነትን ያጠናክራል ይላሉ። ዓዋጁ የኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና የሚወገድበት ከመሆንም ባለፈ ዜጎች በመደመር ፍልስፍና  እየተመሩ በአገራቸው ዕድገት ለመሥራት ያነሳሳቸዋል በማለትም ተናግረዋል። የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ በዳሳ ጅንፈሳ ዓዋጁ ለክልሉ ብሎም ለአገር ልማትና እድገት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።አንድነትና በጋራ መሥራትን እንደሚያበረታታ በመጠቆም። የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አስመራ እጃራ እንዳሉት ዓዋጁ ሕዝቡ በጉልበቱ፣በእውቀቱና በገንዘቡ ድርሻውን እንዲወጣና ራዕይ እንዲኖረው ያደርጋል ባይ ናቸው። የክልሉና የአገሪቱ ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚያስችል ተናግረዋል። የኦሮሚያ ክልል የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር  ቢሮ ኃላፊ  አቶ ቶሎሳ ገደፈ እንደተናገሩት ዓዋጁ ለአገሩና ለክልሉ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ችሎታና ብቃት ያለው ትውልድ ያስችላል። ለአገሩም ሆነ ለክልሉ ተቆርቋሪ ዜጋ በመፍጠርና የሥራ ባህልን በማሳደግ ሕዝቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል። የመንግስት አገልግሎት ተደራሽ ያልሆነባቸው ቦታዎችን በመሸፈን ቀዳዳዎች በመሸፈንና ኃላፊነት የሚሰማውና የዜግነት ግዴታውን በመወጣት አርአያ የሚሆን ዜጋ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል። በነቀምቴ ከተማ ዓዋጁን ለማስተግበር ምክር ቤትም ተቋቁሟል። በከተማዋ ሁለገብ አዳራሽ በተካሄደው ውይይት ላይ ከዞንና ወረዳዎች መሥሪያ ቤቶችና ከከተማው አስተዳደርና ከክፍለ ከተሞች የተውጣጡ አንድ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች  ተሳትፈዋል። ውይይቱ እስከ ቀበሌ ድረስ በተመሳሳይ መልኩ እንደሚካሄድም ተገልጿል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም