የመቐለ ከተማ ምክር ቤት ለ2012 በጀት ዓመት ከ2 ቢሊዮን 766 ሚሊዮን ብር በላይ አጸደቀ

147

መቐለ ሀምሌ  12/2011 የመቐለ ከተማ ምክር ቤት አራተኛ ዘመን 25ኛ መደበኛ ጉባኤውን ለ2012 በጀት ዓመት የሚውል ከ2 ቢሊዮን 766 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በማጽደቅ ተጠናቀቀ።

ለሦስት ተከታታይ ቀናት የተካሄደውና ዛሬ የተጠናቀቀው የከተማው ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በጀቱን ያጸደቀው ለካፒታልና ለመደበኛ ሥራዎች ወጪ እንዲውል ነው።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ለተብርሃን ገበረሰማያት እንዳሉት በጀቱ ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በድጎማ፣ ከዓለም ባንክ በብድር፣ ከመንገድ ፈንድ እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ድጋፍ፣ ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ገቢና ከሌሎች የገቢ ምንጮች የሚገኝ ነው።

በበጀት ዓመቱ በከተማው ውስጥ ከሚከናወኑ የልማት ሥራዎች መካከል 14 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገድ እና ለጤና ተቋማት የሕክምና መሳሪያዎች የሟማላት ሥራ ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም የታክሲና የአውቶቡስ ማቆሚያ፣ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት ግንባታ፣ የተፋሰስ ልማትና ሌሎች የልማት ሥራዎች እንደሚሰሩም አፈጉባኤዋ ገልጸዋል።

የመቐለ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር አርአያ ግርማይ ባቀረቡት የ2011ዓ.ም የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንዳሉት፣ በበጀት ዓመቱ በከተማው ከ23 ሺህ በላይ ሰዎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።

ለ222 ባለሃብቶች ለኢንቨስትመንት የሚውል ቦታ የተሰጠ ሲሆን፣ 308 መካከለኛና አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች እንዲቋቋሙ መደረጉንም ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ለ596 አካልጉዳተኞች ከስምንት ሄክታር በላይ ለመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መሰጠቱንም ኢንጂነር አርአያ አመልክተዋል።

በተጨማሪም በ343 ማህበራት ስር ለተደራጁ ነዋሪዎች ከ58 ሄክታር በላይ ቦታ ለተጠቃሚዎች መተላለፉን ነው የገለጹት።

“በጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ሰዎች 315 ሚሊዮን ብር የብድር አቅርቦት አግኝቷዋል” ያሉት ኢንጅነር አርአያ፣ በተለያዩ ዓመታት በብድር ከተሰጠው ገንዘብ ውስጥ 562 ሚሊዮን ብር አለመመለሱን ተናግረዋል።

በብድር የተወሰደውን ገንዘብ ለማስመለስ የከተማው ምክር ቤት አባላት በ2012 በጀት ዓመት ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ምክትል ከንቲባዋ አሳስበዋል።