የአፍሪካ ኅብረት የኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝን ለመከላከል የህክምና ቡድን ሊልክ ነው

99
ሐምሌ / 2011 ( ኢዜአ)የአፍሪካ ኅብረት የኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝን ለመከላከል የህክምና ቡድን ወደ ስፍራው ሊልክ መሆኑን በኅብረቱ የበሽታ መከላከል ማዕከል አስታወቀ። ከሰሞኑ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወደ ሩዋንዳ በሚወስደው የትራንስፖርት እምብርት በሆነችው 'ጎማ' አነስተኛ ከተማ የኢቦላ ቫይረስ ወረርሺኝ መከሰቱ ይታወሳል። ባለፉት 11 ወራት በተቀሰቀሰው የኦቦላ ወረርሺኝ ከ2 ሺ 500 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል፤ ከእነዚህም መካከል 1 ሺ 700      ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። የቫይረሱ ስርጭት እየሰፋ በመሄዱና ቤኒ፣ ቡቴምቦ፣ ማንዲማ፣ ቩሆቪና ሙትዋንጋ በተሰኙ አካባቢዎች በሽታው በ10 ሰዎች ላይ በመታየቱ ወደ ጎረቤት አገራት እንዳይዛመት ስጋት ሆኗል። ይህን ተከትሎ ከትናንት በስቲያ የዓለም የጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ የጤና እርዳታ አንደሚያስፈልገው ውሳኔ አሳልፏል። የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ወረርሺኙን በማስመልከት "በዓለም አደገኛው ቫይረስ በዓለም አደገኛ ሥፍራ ላይ ተከስቷል"  ብለዋል። የአፍሪካ ኅብረት የበሽታ መከላከል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጆን ኬንጋሶንግ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ማዕከሉ በኮንጎ የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመከላከል ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየሰራ ነው። በተለይም ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና የቫይረሱ ስርጭት ከሚያሰጋቸው የጎረቤት አገራት ጋር በቅርበት የመከላከልና የደህንነት ጥበቃ ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። በቅርቡም በአካባቢው አገራት እንዳይሰራጭ የአፍሪካ ኅብረት በምዕራብ አፍሪካ የተላከውን አይነት የህክምና ቡድን ወደ ሥፍራው በመላክ ርብርብ ይደረጋል ነው ያሉት። በአሁኑ ወቅት ጎማ በምትባለው ከተማ 97 ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውን ጠቁመው እስካሁን 77ቱ ክትባት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል። ማዕከሉም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚያቀርበውን የህክምና መሳሪያዎችና መድሃኒቶች በስፋት እንደሚያዳርስ ገልጸዋል። ድንበር ዘለል የህክምና ምርምራና የቤተ-ሙከራ ሥራዎች እንዲሁም በኮንጎና በጎረቤት አገራት ስለ ስርጭቱ የሚሰጠው የመረጃ ፍሰት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። በኮንጎ የተከሰተው ይኸው ወረርሺኝ በኢቦላ ታሪክ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2014 እስከ 2015 በምዕራብ አፍሪካ ከተከሰተው ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም