የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነገና ከነገ በስቲያ በለንደን ከተማ ይካሄዳል

66
ሐምሌ 12/2011 10ኛ ዙር የ2019 የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነገና ከነገ በስቲያ በእንግሊዝ ርዕሰ መዲና ለንደን ሲካሄድ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ። ነገ በሚካሄደው የ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች ውድድር አትሌት አክሱማዊት አምባዬና አትሌት ዳዊት ስዩም ይሳተፋሉ። አትሌት አክሱማዊት በዘንድሮው የዳይመንድ ሊግ ውድድር እስካሁን በተካሄዱ የ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድሮች 11 ነጥብ በመሰብስብ አምስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን በአንጻሩ አትሌት ዳዊት አምስት ነጥብ በመሰብሰብ 11ኛ ደረጃ ላይ ናት። አትሌት አክሱማዊት አምባዬ ሰኔ 6 ቀን 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 3 ደቂቃ ከ59 ሴኮንድ ከ2 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቷን ማስመዝገቧ ይታወቃል። አትሌት ዳዊት እ.አ.አ በ2014 በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት በተካሄደ የአትሌቲክስ ውድድር 3 ደቂቃ ከ59 ሴኮንድ ከ53 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰአቷን ማስመዝገቧ ይታወሳል። በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች የዳይመንድ ሊግ ውድድር 24 ነጥብ በመሰብሰብ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በነገው ውድድር ላይ አትሳተፍም። በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች የዳይመንድ ሊግ የነጥብ የደረጃ ሰንጠረዥ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ 16 ነጥቦችን በመሰብስብ አራተኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ አትሌት አልማዝ ሳሙኤል አንድ ነጥብ ብቻ አግኝታ የመጨረሻውን 15ኛ ደረጃ ይዛለች። በነገው ውድድር ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ከእንግሊዝ፣ ሞሮኮና ኬንያ አትሌቶች ጋር ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ነገ በአምስት ሺህ ሜትር ወንዶች አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት ይሳተፋል። ሰኔ 28 ቀን 2011 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ሉዛን ከተማ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ የአምስት ሺህ ሜትር ውድድር አትሌት ሐጎስ ሩጫው አንድ ዙር እየቀረውና የመጨረሻው ዙር ደወል እየተደወለ ባለበት ሁኔታ አሸንፌያለሁ ብሎ ደስታውን በሚገልጽበት ወቅት አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ከኋላው ቀድሞት አሸናፊ የሆነበት አጋጣሚ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ እንደነበር ይታወሳል። አትሌት ሐጎስ የቀረውን 400 ሜትር ጨርሶ አስረኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን አትሌቱ ካለው ልምድ አንጻር የሰራው ስህተት ያልተለመደና እንግዳ ነገር እንደሆነ የስፖርቱ ቤተሰቦች ሲገልጹም ነበር። ''በስታዲየሙ የነበሩ ደጋፊዎች ከፍተኛ የድጋፍ ድምጽ ሲሰጡኝ የውድድሩ አሸናፊ የሆንኩ መስሎኝ ነው ደስታዬን ስገልጽ የነበረው'' ሲል ከውድድሩ በኋላ አትሌት ሐጎስ መናገሩ አይዘነጋም። አትሌት ሐጎስ ከሉዛኑ ክስተት በኋላ ነገ በሚካሄደው የአምስት ሺህ ሜትር ውድድር የሚሳተፍ ሲሆን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱንም አግኝቷል። የዚህኛው ዙር የአምስት ሺህ ሜትር ውድድር የዳይመንድ ሊግ ነጥብ አያሰጥም። በዳይመንድ ሊግ የአምስት ሺህ ሜትር የነጥብ የደረጃ ሰንጠረዥ አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ29 ነጥብ አንደኛ አትሌት ጥላሁን ሃይሌ በ18 ነጥብ፣ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በ16 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት 12 ነጥብ ሰብስቦ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከነገ በስቲያ በአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች በሚካሄደው ውድድር አትሌት ለተሰንበት ግደይ የምትሳተፍ ሲሆን እስካሁን በዳይመንድ ሊጉ በተካሄዱ የአምስት ሺህ ሜትር ውድድሮች ስድስት ነጥብ በመሰብሰብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በዳይመንድ ሊግ የአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች የነጥብ የደረጃ ሰንጠረዥ 12 ነጥቦችን በመሰበስብ በአንደኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው አትሌት ገንዘቤ በነገው ውድድር ላይ አትሳተፍም። አትሌት ፋንቱ ወርቁ ሰባት ነጥቦችን በመሰብሰብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በነገው ውድድር በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችው ሲፋን ሀሰን የማሸነፉን የቅድሚያ ግምት አግኝታለች። ነገና ከነገ በስቲያ በለንደን ስታዲየም የዳይመንድ ሊግ ነጥብ የሚያሰጡ የተለያዩ የአትሌቲክስና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ይካሄዳሉ። 11ኛ ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነሐሴ 12 ቀን 2011 ዓ.ም በእንግሊዝ በርሚንግሀም ከተማ ይካሄዳል። በአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያና ሰሜን አሜሪካ በሚገኙ 14 ከተሞች የሚካሄደው ዳይመንድ ሊግ ጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም በቤልጂየም ርዕሰ መዲና ብራሰልስ በሚካሄደው ውድድር ይጠናቀቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም