የፈረንሳይ የኢኮኖሚና የገንዘብ ሚኒስትር ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው

43
አዲስ አበባ ኢዜአ ሀምሌ 12/2011 የፈረንሳይ የኢኮኖሚና የገንዘብ ሚኒስትር ብሩኖ ሊሜር የፊታችን ሰኞ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ። የሚኒስትሩ ጉብኝት የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መጋቢት 3 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የተዘጋጀ መሆኑን በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የፈረንሳይ የኢኮኖሚና የገንዘብ ሚኒስትር ብሩኖ ሊሜር በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ከገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ጋር እንደሚወያዩም ተገልጿል። ውይይቱ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት አገራቱ በተለያዩ ዘርፎች የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች ወደ ትግበራ መቀየር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ እንደሚያተኩር ኤምባሲው ገልጿል። ብሩኖ ሊሜር ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ከሚያደርጉት ውይይት በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንደሚጉበኙም ታውቋል። የ50 ዓመቱ ሚኒስትር ከግንቦት 2009 ዓ.ም ጀምሮ የፈረንሳይ ኢኮኖሚና የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ። የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መጋቢት 3 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ሁለቱ አገራት በመከላከያ፣ በህዋ ሳይንስ፣ በኢኮኖሚና በሌሎችም ዘርፎች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው። ማክሮን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትንም የጎበኙ ሲሆን 2011 ዓ.ም ፈረንሳይ ለአብያተ ክርስቲያናቱ ጥገናና ድጋፍ እንደምታደርግም መግለጻቸው ይታወቃል። ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1897 ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም