በጋምቤላ ክልል አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ ቅሬታዎችን ለመመለስ ያደረጉት ጥረት አበረታች ነበር - ቋሚ ኮሚቴዎች

94
ጋምቤላ ኢዜአ ሐምሌ 12 ቀን 2011 በጋምቤላ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ ቅሬታዎችን ለመመለስ ያደረጉት ጥረት አበረታች እንደነበር የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ገለጹ፡፡ የበጀት ዓመቱ አፈፃፀም በጋምቤላ ከተማ ተገምግሟል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ለኢዜአ እንዳሉት በ2011 በጀት ዓመት የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመመለስ ከአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ጋር ቅንጅታዊ ሥራዎችን በማጠናከር በኩል የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል፡፡ በተለይም ቋሚ ኮሚቴው ከሕዝቡ የተነሱ ቅሬታዎችን ከአስፈጻሚ አካላት ጋር በየሩብ ዓመቱ በመገናኘት ክትትልና ግምገማ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ እንደ ቋሚ ኮሚቴዎች ገለጻ በበጀት ዓመቱ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እንዲሁም በፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት ዙሪያ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በምክር ቤቱ የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኡኬሎ ኡማን እንዳሉት በክልሉ የዜጎችን መብት በማስከበርና ታራሚዎችን በይቅርታ ከማስፈታት ጀምሮ የሕግ የበላይነትን የሚያስከብሩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በተለይም ቋሚ ኮሚቴው የአስፈጻሚ አካላትን የማስፈጸም አቅም በመገምገም የአመራር ለውጥ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም በበጀት ዓመቱ የታዩ ጠንካራ ሥራዎችን በማስቀጠልና ክፍተቶች በማረም በተለይም የሕግ የበላይነትን በማስፈን በትኩረት እንደሚሰራም  ሰብሳቢው አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ስኬታማነት የአስፈጻሚ አካላት ሚና መጠናከር እንዳለበትና ሕዝቡም የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማቅረብን መለማመድ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ምክር ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ወይናቱ አበራ እንደተናገሩት ቋሚ ኮሚቴው ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ መወያየቱን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ከፍጆታ ዕቃዎች ክፍፍል ጋር ተያይዞ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች ለመፍታት በባለሀብቶች እጅ የነበረውን የማከፋፈል ሥራ ለተደራጁ ወጣቶች መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም ከስኳር፣ ከዘይትና ከዳቦ ዱቄት ተደራሽነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የቁጥጥር ስራውን ለማጠናከር ከክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ጋር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ በበኩላቸው በክልሉ የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ሕይወት ለማሻሻልና ምርታማነትን ለማሳደግ ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጠውን የመስክ ግምገማ መሰረት በማድረግ በመሰራቱ የተሻለ ክንውን መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በበጀት ዓመቱ በማህበራዊ ዘርፍ  በተለይም በጤናና በትምህርት ዘርፎች ያለው ክንውን አሁንም ክፍተቶች እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ካን ጋልዋክ በክልሉ የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት፣በኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከል እንዲሁም ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ ክፍተቶች መታየታቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ችግሮቹን ለማቃለል በማህበራዊ አገልግሎት ዙሪያ ያለውን ቅሬታ ለመፍታት ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም