የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መንገደኞችን በማስተናገድ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዘገበ

293

ሐምሌ 11/2011 የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በትናንትናው እለት ብቻ ከቀደሙት ጊዜያት ከፍተኛ ቁጥር ያለው መንገደኛ በማስተናገድ ክብረ ወሰን ማመዝገቡን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።

አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ትናንት ሃምሌ  10 ቀን  2011 ዓም በከፍተኛነቱ በአየር ማረፊያው ታሪክ ያልተመዘገበ መንገደኛ ተስተናግዷል።

በእለቱ 29 ሺህ 528 ሺህ ተጓዦች በ310 በረራዎች በአየር ማረፊያው ተስተናግደዋል።

ከእነዚህ መንገደኞች መካከል 21 ሺህ 28ቱ ከአዲስ አበባ ወደሌሎች ከተሞች የበረሩ ሲሆን የተቀሩት 8 ሺህ 500 ከሌሎች ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ የደረሱ ናቸው።

ይህም የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የመንገደኛ ማስተናገጃ ተርሚናል በአንድ ቀን ያስተናገደው ክብረ ወሰን የሆነ ቁጥር እንደሆነም ተመልክቷል።

የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ተጠባባቂ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌታነህ አደራ ” አዲሱ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች ማስፋፊያ ፕሮጀክት በቅርቡ በከፊል ለአገልግሎት መብቃቱን ተከትሎ በአንድ ቀን ውስጥ ክብረ ወሰን የሆነ ተጓዦች በመስተናገዱ በጣም ተደንቀናል” ብለዋል።

በአፍሪካ ግዙፉ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት ከ130 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሉት።

የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያም በቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎችን ያስተናግዳል።

ባለፈው ጥር ወር 2011 ዓ.ም ከተመረቀው ማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በተጨማሪ አየር ማረፊያው በቀጣይ የሚያካሄዳቸው የማስፋፊያ ስራዎች ዓመታዊ የመንገደኞች ማስተናገድ አቅሙን ወደ 22 ሚሊዮን ለማድረስ እንደሚያስችለው በመግለጫው ተጠቅሷል።

የተመረቀው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል የማስፋፊያ ግንባታ በሙሉ አቅሙ ወደስራ ሲገባ ዘመኑ የደረሰባቸው የአየር ማረፊያ መሳሪያዎችና የመንገደኞች አገልግሎት መስጫዎች ይኖሩታል ተብሏል።

ባለፈው ዓመት አዲስ አበባ፤ ዱባይን በመቅደም ረጅም ርቀት በአየር ላይ ተጉዘው ወደአፍሪካ የሚገቡ ተጓዦችን በከፍተኛ ሁኔታ በማስተናገድ ዋንኛ የትራንስፖርት መዳረሻ ሆና የተመዘገበች መሆኑንም የአየር መንገዱ መግለጫ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥር 19 ቀን 2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማትና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት 363 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበትን የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል የማስፋፊያ ፕሮጀክት ማስመረቁ የሚታወስ ነው።