ፓርቲው የአፋር ሕዝብ በክልሉ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ውጤታማ ለማድረግ ከጎኑ አንዲቆም ጠየቀ

56
ሰመራ ሐምሌ 11 ቀን 2011 የአፋር ሕዝብ በክልሉ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ውጤታማ ለማድረግ ከጎኑ አንዲቆም የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አብዴፓ/ጠየቀ። ፓርቲው ለከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ በሰመራ ከተማ ተጀምሯል። የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ፓርቲው የሕዝቡን የለውጥ ፍላጎትና ጥያቄዎች ለመመለስ እያደረገ ያለውን ጥረት በተሳትፎው መደገፍ ይጠበቅበታል። ለዚህም የአገር ሽማግሌዎች ፤ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም ምሁራን የሕዝቡን እርካታ የሚፈጥር፣አገልጋይና አመራር ሰጪ እንዲሆን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል። ፓርቲው የሕዝቡን የለውጥ ፍላጎት መሠረት በማድረግ የአመራር ለውጥ ካደረገ ሰባት ወራት ማስቆጠሩን አስታውሰው፣ እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ ጥራትና ብቃት ያላቸው አመራሮች መመደባቸውን ገልጸዋል። ለውጡ የኅብረተሰቡን የልማት ጥያቄ የሚመልስ፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አንዲሁም ከአድልኦ የጸዳ አሰራር አንዲሰፍን በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች ኃላፊነታቸውን በትጋት እንዲወጡ ኢንጂነር አይሻ አስገንዝበዋል። የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዓሊ ሁሴን ''የክልሉ የለውጥ ጉዞ- ስኬቶችና ፈታኝ ሁኔታዎች'' በሚል ርዕስ ባቀረቡት መነሻ ጽሁፍ ፓርቲው የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ እያደረገ ያለው ጥረት ሂደቱን የሚያጓትቱና በታሰበው ፍጥነት እንዳይሄድ የሚያደርጉ ፈተናዎች እንደገጠሙት አስረድተዋል። ከነዚህምለውጡንየማይፈልጉኃይሎችፓርቲውየክልሉንየአመራርለውጥባደረገበትማግስትጀምሮከሌላማህበረሰብእንዲጋጭሙከራማድረጋቸውንአንስተዋል። በተጨማሪም መንገድ መዝጋትና ተያያዥነት ያላቸው ሙከራዎች ለውጡን ለማደናቀፍ መሞከራቸውንም አቶ ዓሊ አስረድተዋል። ይሁንና ፓርቲው ችግሮቹን ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን በብልጠትና ትዕግስት በተሞላበት ሁኔታ ማለፉን ገልጸዋል። በቀጣይም ኅብረተሰቡ ከጎሰኝነትና ቡድንተኝነት አስተሳሰብ ተላቆ አመራሮችን በብቃታቸውና በሥራ አፈጻጸማቸው በመለካት አንድነቱን ማስቀጠል ይኖርበታል ብለዋል። በስልጠናው ላይ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው። አብዴፓ የአፋር ክልል ገዢ ፓርቲ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም